ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ በጥናት ላይ የተመሠረተ የአቅም ግንባታ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።
ብሾፍቱ # ጥር 01/2018 ዓ/ም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር የአቅም ግንባታ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት የሚያስችልና መሠረት የሚሆን የፍላጎት መገምገሚያ እና ግብዓት መሠብሰቢያ /need assessment /የዘርፉን ሀላፊዎችንና ከፍተኛ ባለሙያዎችን ያሳተፈ ወርክሾፕ በፒራሚድ ሆቴል እየተካሄደ ነው።
የመርሃግብሩን ይፋዊ መጀመር የገለጹት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ አቅምን ገንብቶ ወደ ስራ መግባት ወሳኝ እንደሆነ ገልፀው ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የአቅም ግንባታ ማዕቀፍ የፍላጎት ግብዓት መሰብሰቢያ /need assessment /ወርክ ሾፕ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
አቶ ደበበ አክለው ማዕቀፉ አስፈላጊው ግብዓት ተሰብስቦና ተዘጋጅቶ ወደ ስራ ሲገባ የተመደበው ሀብት በትክክል ስራ ላይ እንዲውልና ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።
ለማዕቀፉ ዝግጅት አስፈላጊውን ግብዓት ለመሰብሰብ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያሉና በፕሮጀክቶች ላይ ዕምቅ አቅምና ዕውቀት ያላቸውን ሀላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሳተፉ የተደረገው ጉዳዩ ወሳኝና ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ነው ያሉት አቶ ደበበ ተሳታፊዎች ለውይይቱ ትኩረት እንዲሰጡና አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ተማጽነዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዜርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ የባዜርኔት ፕሮጀክት 5 ኮምፖኔንቶችን እንደሚይዝ ገልፀው የአቅም ግንባታ ኮምፖነንት 5ኛ እና ወሳኝ እንደሆነና 4ቱ ኮምፖነንቶች ተግባራዊና ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያግዝ በመሆኑ መርሃግብሩ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
የሚዘጋጀው የአቅም ግንባታ ማዕቀፍ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ሁሉ መሠረታዊና ወሳኝ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሞላ ፕሮጀክቶች እንደአውዳቸውና እንደ ተጨባጭ ሁኔታቸው ከማዕቀፉ እየቀዱ መጠቀም እንደሚችሉ አብራርተዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሉዴል ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር አለልኝ ዘሩ አጠቃላይ ማዕቀፉ ምን ምን ጉዳዮችን መያዝ እንዳለበት ፣ምን ዓይነት ግብዓቶች መቅረብ እንዳለባቸውና ከፌዴራል ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር አተገባበሩ ምን መሆን እንዳለበት የሚያሳይ ምክረ ሀሳብና አቅጣጫ ጠቋሚ ሰፋ ያለ መወያያ ሰነድ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።
በቀረበው ሰነድ ላይ ተሳታፊዎች በቡድን በስፋትና በጥልቀት በመወያየት ለሚዘጋጀው የአቅም ግንባታ ማዕቀፍ አስፈላጊውን ግብዓት ለማቅረብ ችለዋል ።