የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ የተመረጠው የወዴቻ ንዑስ ተፋሰስ በባለድርሻ አካላት ተጎበኘ።
ቢሾፍቱ : ታህሳስ 16/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ጋር በጋራ በሚተገበረው የብሬይት ፕሮጀክት የወዴቻ ንዑስ ተፋሰስ ላይ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ የዳሰሳ ጥናት እና የ10 አመት እቅድ ተዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበታል።
የቀረበውን የዳሰሳ ጥናት መሠረት በማድረግም መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እና አሉ የተባሉ ችግሮችን ባለድርሻ አካላት በስፍራው ተገኝተው ተመልክተዋል።
በስፍራው ያነጋገርናቸው በውሃና መሬት ሀብት ማዕከል የውሃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት አቶ ደርበው ሻንቆ በነበረው ውይይት መሬት ላይ አሉ ተብለው የተለዩ ችግሮች በተጨባጭ መኖራቸውን ለማረጋገጥ ከፌደራል ፣ከክልል ፣ ከዞን ፣ከወረዳ እንዲሁም ከአርሶ አደሮችና ወጣቶች የተውጣጣ ቡድን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በስፍራው ተገኝተው እንዲመለከቱ ታላሚ ያደረገ ጉብኝት ነው ብለዋል።
በተፉሰሱ ውስጥ በፈረንጆቹ 1980 ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ የነበረው የበልበላ ግድብ አሁን ላይ በደለል እየተሞላና ውሃው እየደረቀ ያለበትን ሁኔታ ባለድርሻ አካላቱ ተመልክተው የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ማድረግ የጉብኝቱ አላማ ነው ብለዋል።
የክረምቱ ዝናብ በግድቡ ተጠራቅሞ ለሚፈለገው አላማ እንዲውል ግድቡ መጠገን እንደሚገባው እና ውሃው ሲደርቅ አርሶአደሮች የሚያርሱበትን ሁኔታ ለመቆጣጠር የውሃ አካላት ደህንነት ጥበቃ (የበፈር ዞን ) ህግን ተግባራዊ ማድረግም ያስፈልጋል ብለዋል።
ቦታው ላይ ጥምር እርሻን ተግባራዊ በማድረግ ማለትም ሳሮችን እና የፍራፍሬ ዛፎችን በመትከል የአፈሩ ደህንነት ተጠብቆ ውሃውም ሳይደርቅ የአካባቢውን አርሶ አደር ተጠቃሚ ማድረግ የ10 ዓመቱ እቅድ አላማ ነው ብለዋል።
ትልቁ ነገር የአካባቢውን አርሶ አደር ግንዛቤ ማስጨበጥ በመሆኑ ውሃው ምን ያህል እንደሚጠቅማቸው ስለሚያውቁ በማነቃቃት ህጉን እንዲተገብሩና በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቁ እንዲሁም ውሃውን በፍትሃዊነት ተጠቅመው እንዲያለሙ ማድረግ ነው ብለዋል።
በአካባቢው ከ30 ዓመት በላይ የኖሩት አቶ ተሾመ ስለሺ የበልበላ ግድብ ጥበቃና እንክብካቤ ስላልተደረገበት ላለፉት አራት ከመታት በደለል እየተሞላ እና ውሃው እየደረቀ መምጣቱን ጠቅሰው ግድቡ ታድሶ ጥበቃና ከለላ ቢደረግለት ውሃው ሳይደርቅ ለረጅም ጊዜ የምናለማበትን ሁኔታ ይፈጥርልናል፤ ተጠቃሚም እንሆናለን ሲሉ ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል።