በስድስት ከተሞች በሚገነባው ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያና ማስወገጃ ፕሮጀክት የትግበራ ሂደት ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ምክክር ተካሄደ፡፡
ታህሳስ 15/2018 ዓ.ም.(ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሶስት ክልሎች ስር በሚተዳደሩ ስድስት ከተሞች ለሚገነባው ዘመናዊ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያና ማስወገጃ ፕሮጀክት(Faecal Sludge and Septage Treatmenet Plant) የግንባታ ሂደት የባለድርሻ አካላት ምክክር ተካሄደ፡፡
የምክክር መድረኩን የመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ሲሆኑ በጽህፈት ቤታቸው በሚገኘው የስብሰባ አዳራሽ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አወያይተዋል፡፡
አክለውም በተለይም በአሁኑ ወቅት በመንግስት ትኩረት የተሰጠው ከተሞችን የማልማትና አረንጓዴና ፅዱ አካባቢን ከመፍጠር ተልዕኮ ጋር የተሳሰረ ቁርኝት ያለው በመሆኑ ከየቤቱ የሚወጣ ፍሳሽ ቆሻሻን በአግባቡ ለማስተዳደርና መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚቻልበትን ሳይንሳዊ መንገድ በማመቻቸት የሚተገበር በመሆኑ ይህንን ተግባር እንደምሳሌ በመውሰድ ወደ ሌሎች ከተሞች ለማስፋፋትም ብርቱ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በሃገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሳኒቴሽን መሰረተ ልማት በብድር አቅርቦት ግንባታ ለማካሄድ የተጀመረ ሲሆን በአማራ ክልል (እንጂባራና አረርቲ)፣በኦሮሚያ(ፊቼና ቡራዩ)እንዲሁም በማአከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቡታጂራና ሆሳዕና ከተሞች ላይ የሙከራ ትግበራ እየተደረገ መሆኑን የሚያስገነዘብ ለውይይት መነሻ የሚሆን ገለጻ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የፕሮጀክቱ አስፈጻሚ ቡድን ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የፕሮጀክቱ የፋይናንስ አፈጻጸም፣ ከወሰን ጋር የተገናኙ ጥያቄዎች፣የፕሮጀክት መዋጮ፣የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ መኪና ግዢና ሌሎች ከፕሮጀክቱ አፈጻጸም ጋር ሊገጥሙ የሚችሉ ስጋቶች የተነሱ ሲሆን የሚፈቱባቸው ዘዴዎችም አቅጣጫ ተሰጥቶባቸዋል፡፡