የዳሳሳ ጥናቱ ግኝትና ምክረ ሀሳብ መሬት ወርዶ ተግባራዊ ከሆነ የፕሮጀክቱ ዋና ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።

የዳሳሳ ጥናቱ ግኝትና ምክረ ሀሳብ መሬት ወርዶ ተግባራዊ ከሆነ የፕሮጀክቱ ዋና ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። ባህርዳር # ታህሳስ 15/2018 ዓ/ም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል /Water and Land Resource Cente WLRC/ ጋር በመተባበር በብራይት /BRIGHT/ ፕሮጀክት አመቻችነትና አሳላጭነት በኢንፍራንዝ ንዑስ-ተፋሰስ የዳሰሳ ጥናትና የተፋሰስ ልማት ዕቅድ ላይ ለ3 ተከታታይ ቀናት ባህርዳር ከተማ ሲካሄድ የነበረ የባለድርሻ አካላት ወርክሾፕ ዛሬ ተጠቃሏል።   በማጠቃለያው መርሃግብር ላይ የተለያዩ የኢንፍራንዝ-ንዑስ ተፋሰስ በሚያካልልበት አካባቢዎች ባሉ ጭብጦች ዙሪያ በዘርፉ ባለሙያዎች በቀረቡ የዳሰሳ ጥናቱ ግኝቶችና ምክረ- ሀሳቦች ላይ ተሳታፊዎች በርካታ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን አንስተው ጠለቅ ያለ የቡድንና የጋራ ውይይት ተደርጎባቸዋል፣ የመፍትሄ ሀሳቦችም ተቀምጠዋል። የውይይት መድረከኩን ሲመሩና ሲያወያዩ የነበሩት የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል /WLRC/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጠና አላምረው ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ፣ ማብራሪያና ለተግባራዊነቱና ለውጤታማነቱ ጠቃሚ ምክረ ሀሳብ አቅርበው ለፕሮጀክቱ ውጤታማነትና ተግባራዊነት ሁላችንም በባለቤትነት ስሜት በትብብርና በቅንጅት ትኩረት ሰጥተን በመስራት ህብረተሰባችንን ተጠቃሚ ማድረግ አለብን ብለዋል።   በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ብዙነህ አስፋው በበኩላቸው በቀረበው የተፋሰስ ልማት ዕቅድ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሰፊ ማብራርያና ምላሽ ከሰጡ በኋላ ለአተገባበሩ የሚያግዝ የወደፊት አቅጣጫ ጠቋሚ ቀና ሀሳቦችንም አቅርበዋል። የባህርዳር ዙሪያ ወረዳ የወገልሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አቶ ሞላ አሸብር እና የሰሜን ሜጫ ወረዳ የቁርጥ ባህር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አቶ ምንአለ ባንቴ በበኩላቸው በአውደ-ጥናቱ ላይ ተሳታፊ በመሆናቸው በብዙ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀው በኢንፍራንዝ-ንዑስ ተፋሰስ ላይ የተሰራው የዳሳሳ ጥናት ግኝትና ምክረ ሀሳብ መሬት ወርዶ ተግባራዊ ከሆነ የፕሮጀክቱ ዋና ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።   አርሶ አደሮቹ አክለው ከወርክሾፑ የውሃ አካለት አጠባበቅ ፣የአፈር መሸርሸርን ከመከላከል፣የአየር ለውጥ ተጽዕኖ ከመመከትና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንፃር ያገኙት ግንዛቤ የፕሮጀክቱ ቀዳሚ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው በመግለፅ ለአካባቢው ህብረተሰብ ያገኙትን ግንዛቤ በማስተላለፍ በባለቤትነት ስሜት ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት እንደሚተጉ ተናግርዋል።

Share this Post