በአዋሽ ተፋሰስ የወዴቻ ንኡስ ተፋሰስ የዳሰሳ ጥናትና የተፋሰስ አስተዳደር እቅድ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

በአዋሽ ተፋሰስ የወዴቻ ንኡስ ተፋሰስ የዳሰሳ ጥናትና የተፋሰስ አስተዳደር እቅድ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው። ታህሳስ 13/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ጋር በጋራ የሚተገበረውና የብራት ፕሮጀክት አካል በሆነው በአዋሽ ተፋሰስ የወዴቻ ንኡስ ተፋሰስን ለማልማት በተካሄደው የዳሰሳ ጥናትና የአስተዳደር እቅድ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።   የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ የውሃ ሀብት አስተዳደሩ ለመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ ለሌሎች ልማቶችም ወሳኝና መሠረታዊ በመሆኑ በጋራና በቅንጅት ማልማት ፣መጠበቅና መንከባከብ ግድ ይላል ሲሉ በመክፈቻ ንግግራው ገልጸዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፉ የውሃ ሀብቱን ለመጠበቅ ከሚሰራባቸው አንዱ የብራይት ፕሮጀክት ነው ያሉት አቶ ደበበ ፕሮጀክቱ የአዋሽ ፣ አባይ ፣ስምጥ ሸለቆ፣ ኦሞ ጊቤ ተከዜ ተፋሰሶችን በማልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በጥናት ላይ ተመስርቶ በቅንጅት የሚተገበር ነው ብለዋል።   በአዋሽ ተፋሰስ የወዴቻ ንኡስ ተፋሰስ ልማት በርካታ ችግሮችን በሚፈታና ለሌሎች ተፋሰሶች ማሳያ እና መነሻ ሊሆን በሚችል መልኩ በተቀናጀ ሁኔታ የሚተገበር ነው ፤ ለዚህ ደግሞ በአዋሽ ተፋሰስ ውስጥ በርካታ እድሎች አሉ ብለዋል። ስራው በርካታ ሴክተሮችን ወደ አንድ ማምጣትን የሚጠይቅ በመሆኑ በጋራ ሆነን ንቅናቄውን በመምራትና በማስተባበር ውጤታ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።   የውይይቱ አላማም ችግሮችን በሚገባ በማየት ፣ ዋና ዋና ጉዳዮችን በቅደም ተከተል በማስቀመጥ በአጭር ጊዜ ተጨባጭ ለውጥ የምናመጣበትን አሰራር ተግባራዊ በማድረግ ለህብረተሰቡ የሚጠቅም ጥንቃቄ የተሞላበት ስራ እንዲሰራ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።   ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉ የኒዘርላንድስ ኤምባሲና ለአውሮፓ ህብረት እንዲሁም ጥናቱን ላደረጉ አካላትና የውይይት መድረኩን ያዘጋጁ ውሃና መሬት ሀብት ማእከልን አቶ ደበበ አመስግነዋል። የውሃና መሬት ሀብት ማእከል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌጤ ዘለቀ የብራይት ፕሮጀክት በአምስቱ ተፋሰሶች ላይ ሲተገበር ያለንን ሀብት በመጠቀም እንዴት ራሳችንን ማስተዳደር እንደምንችል የሚያግዝ ነው ብለዋል።   አቅም ማጎልበት፣ የተቀናጀ የተፋሰስ የመረጃ ስርዓት መተግበር፣የተፋሰስ አያያዝ እቅድ በማዘጋጀት መተግበር እንዲሁም ተሞክሮ የሚሆኑ ንዑስ ተፋሰሶችን መርጦ ውጤታማ ሰራ መስራት የፕሮጀክቱ የትኩረት አቅጣጫ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ እቅዱ ተግባራዊ የሚሆነው በየደረጃው ያለው አካል ማህበረሰቡን ጨምሮ በቁርጠኝነት መስራት ሲቻል መሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።   የወዴቻ ንዑስ ተፋሰስ ሲመረጥ ለአዲስ አበባ ቅርብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ባለስልጣናት የሚጎበኙበትን እድል ያሰፋል ፤ ለዚህ ደግሞ ንዑስ ተፋሰሱ በሚጠበቀውና በሚፈለገው ልክ መልማት አለበት ብለዋል። በውይይቱ ከፌደራል ፣ ከክልል ፣ከወረዳ ፣ ከተፋሰስ ጽ/ቤት ፣ከምርምር ተቋማት እና ከማህበረሰብ ተወካዮች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት በቀረበው የዳሰሳ ጥናትና በእቅዱ ዙሪያ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።

Share this Post