በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ ተግባራዊ ለሚደረገው የተቀናጀ ስራ ምቹ ሁኔታ መኖሩ ተገለጸ።
ጅግጅጋ ህዳር 21/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በባዘርኔ ፕሮጀክት የሚተገረውን የተቀናጀ ስራ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩ ተገልጿል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሰሞኑ በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ በባዘርኔት ፕሮጀክት ተግባራዊ የሚደረገውን የተቀናጀ ስራ የነባራዊ ሁኔታ ግምገማ ሪፖርትን ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ይህንን አስመልክቶ ለስራው የተመረጡ አካባቢዎች ተጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ያነጋገርናቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ ፕሮጀክቱ በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ በተመረጡ ሁለት ቦታዎች ማሳያ ሊሆን በሚችል መልኩ የመረጃና የውሃ አጠቃቀም ስርዓትን፣ የኢነርጂ አቅርቦትን፣ የበፈር ዞን፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የአፈርና ውሃ እቀባ ስራዎችን በማስተሳሰር ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
በፕሮጀክቱ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ ለውጥን የመቋቋም አቅም እንዲፈጠር እና የማህበረሰቡ የንሮ ደረጃ እንዲሻሻል ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።
በተመረጡ ቦታዎች የአካባቢ ጥበቃ ስራውን ማሳያ ሊሆን በሚችል መልኩ በውጤታማነት ለመተግበር በቂ አቅም እንዳለም ነው አቶ ደበበ የገለጹት።
በቅድመ ዝግጅት ስራዎችም ጥናት በማካሄድና መረጃ በመሠብሰብ እንዲሁም ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን በማስተካከል ወደ ትግበራ ለመግባት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯልም ብለዋል።
በፕሮጀክቱ በ528 ሄክታር መሬት ላይ የአረንጓዴ ልማትን ተግባራዊ ለማድረግ ችግኝ የማፍላት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
ስራው በተሻለ አቅም ወደ ሌሎች ተፋሰሶች እንዲሰፋ፣ ሌሎች ግንዛቤ እንዲያገኙና ጥቅሙን እንዲረዱ ማሳያ ሊሆን በሚችል መልኩ ይተገበራል ብለዋል።
በቀጣይ የሚተገበሩ ስራዎችን አስመልክቶ የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንደሚሰሩም ነው አቶ ደበበ የገለጹት።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ በምስራቅ ሀረርጌ በባቢሌ ወረዳ የኢፋዲን ንኡስ ተፋሰስ እንዲሁም በሱማሌ ክልል ቀላፎ ወረዳ አልጎሪስ ንዑስ ተፋሰስ ላይ በቀጣይ ሶስት ዓመታት የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስራዎች ይተገበራሉ ብለዋል።
ፕሮጀክቱን መሬት ላይ ለማውረድ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹት አስተባባሪው ለውጤታማነቱ ከአመራሩ ጀምሮ እስከታችኛው ማህበረሰብ ያለው ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ለስራው ውጤታማነት በእጅጉ ጠቃሚ ነው ብለዋል።
የተፋሰስ ስራውን ለማስጀመር ከየወረዳዎቹ ጋር በመነጋገር የችግኝ ማፍላት ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ሚያዚያ ላይ የተከላ ስራው እንደሚከናወንም ነው አክለው የገለጹት።
የባዘርኔት ፕሮጀክት በጣሊያን ትብብር የ31.5 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ በአዋሽ፣ ደናክልና ዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች የሚተገበር ሲሆን በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ ሊለሙ በተመረጡ ሁለቱ ንኡስ ተፋሰሶች ላይ ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለቀጣይ ሶስት አመታት ተግባራዊ ሲደረግ የተፋሰስ ልማት ስራው እያደገና እየተጠናከረ ይሄዳል ብለዋል።
የተፋሰስ ልማት ስራው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ፣ ከግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ ፣መስኖ፣ ማእድን ፣ ከአካባቢው ማህበረሰብ እና ሌሎች ከሚመለከታቸው ሴክተሮች ጋር በቅንጅት ተግባራዊ ይደረጋል።