የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ሙስናን ለመከላከል መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ባከናወነው ተግባር ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገለጹ
ህዳር /19/2018 ዓ.ም(ሚ.ው.ኢ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር 'ትውልድን በስነ-ምግባር፥ ተቋምን በአሠራር' በሚል መሪ ቃል 22ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን በድምቀት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ ክቡር ሚኒስትር፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ተወካዮች እንዲሁም የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች ተገኝተዋል።
በዓሉን አስመልክቶ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስተር ክቡር ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ፤ ሙስና ለዘመናት የሀገር ዕድገት ማነቆ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ሙስናን ለመከላከል መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ባከናወነው ሰፊ ተግባር ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ለዚህ ውጤት መመዝገብ በዋነኝነት የሚጠቀሠው የተቋማት አሠራር በሪፎርም እንዲቃኝ መደረጉ እንደሆነ ገልፀዋል።
አክለውም በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ በተደረገ ሪፎርም አመርቂ ውጤት ተገኝቷል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ፤ ቅጥርን በጥብቅ ዲስፕሊን የሚመራ የውድድር ስርዓት መዘርጋቱን በአብነት አንስተዋል።
በተጨማሪም አሠራርን ዲጂታላይዝ ማድረግ፣ ምቹ የስራ ከባቢን መፍጠር እና የጨረታ ስርዓቱን ከብልሹ አሰራር የፀዳ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
እንደ ዘርፍ ስራችንን ስናከናውን የስራ እና የሙያ ስነ-ምግባር ጠብቀን ከሙስናና ብልሹ በፀዳ መሆን አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
የፌደራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አቶ ፍቃዱ ሰቦቃ በበኩላቸው፤ የሀገራችንን የማሠራራት ጉዞ በሁሉም መስክ ለማስቀጠል መስራት ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ዘመኑን የሚመጥን በአሠራር የዘመነ ተቋማትን መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ትውልዱ በትልቅ ኃላፊነት ለመጪው ትውልድ ከሙስናና ብልሹ አሠራር የፀዳች ሀገር ለማስረከብ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በዓሉን አስመልክቶ የውይይት መነሻ በድምፅ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል እንዲሁም በዘርፉ የከፍተኛ አመራሮች የሀብት ምዝገባ ተካሂዷል።