በባዘርኔት ፕሮጀክት የሚተገበረው የዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ የነባራዊ ሁኔታ ግምገማ ሪፖርት ላይ ውይይት ተደረገ።
ጅግጅጋ ህዳር 18/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በባዘርኔት ፕሮጀክት የሚተገበረውን የዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ የነባራዊ ሁኔታ ግምገማ ሪፖርት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
የውይይቱን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውሃን በተመለከተ በርካታ ስራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው ባለፉት ሶስትና አራት አመታት የውሃው ዘርፍ በራሱ ተደራጅቶ እንዲመራ መደረጉ ለውጤቱ አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።
በባዘርኔት ፕሮጀክት የታቀፉ ተፋሰሶች ላይ በርካታ ሰራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ይህን ትልቅ እድል በመጠቀም እያንዳንዱ ባለድርሻ አካላት ስራውን አጠናክሮ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በፕሮጀክቱ የሚጠበቀው እና የሚፈለገው ተጨባጭ ውጤት ፣ መሬት ላይ የሚተገበረው የሚቆጠር ስራ እና የመጣው ለውጥ በሚገባ ተቀምሮ መቀመጥ ስላለበት በዚህ ልክ ሁሉም አውቆ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል ፤ የዛሬው መድረክም ይህንን መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል ክቡር አቶ ሞቱማ።
ለውሃ ሀብታችን ትኩረት ካልሰጠን መጠጥ ውሃ ላይም ሆነ ኢነርጂው ላይ የምንሰራው ስራ ውጤታማ ሊሆን አይችልም ያሉት ክቡር አቶ ሞቱማ የውሃ ሀብቱን መንከባከብ፣ መጠበቅ እና በአግባቡ ማስተዳደር ወሳኙና የመጀመሪያው ስራችን መሆኑን አውቀን እየሠራን ነው ብለዋል።
እንደ ሀገር ባሉን 12 ተፋሰሶች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ወሳኝነት ስላለው አባይ ፣ አዋሽ ፣ኦሞ እና ሪፍት ቫሊ ላይ እየተሰራ ያለውን ስራ ወደ ሌሎች ተፋሰሶች አስፍቶ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል።
የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ ( Italian agency for development copration ) የዋሽ፣ ኢንቫሮመንት እና ኢነርጂ ሴክተር ማናጀር ሚስተር ፋቢዎ ጋጊ (FABIO GAGGI) የባዘርኔት ፕሮጀክት በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም የአካባቢውን ማህበረሰብ የንሮ ደረጃ ለማሻሻል ትኩረት አድርጎ እየተተገበረ ነው ብለዋል ።
ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ የሚሰራው ስራ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማስፈን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ በተፋሰሱ አካባቢ ለሚኖሩ ማህበረሰቦችም ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
የባዘርኔት ፕሮጀክት ውጤታማነት በበጀት ላይ የተመረኮዘ ብቻ ሳይሆን ተገቢውን ቴክኒካል ዲዛን ከመቅረጽ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ አካላት ትብብርና ቀጣይነት ያለው ተሳትፎን የሚጠይቅም ነው ብለዋል።
በጣሊያን ትብብር በ31.5 ሚሊየን ዩሮ የሚደገፈው የባዘርኔት ፕሮጀክት የውሃ ማፋሰሻን በመገንባት ፣በመጠገንና የመቋቋም አቅምን በማሻሻል ችግሩ በስፋት በሚከሰትባቸው ቦታዎች ላይ እንደሚተገበርም ነው ሚስተር ፋቢዮ የገለጹት።
የዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ የነባራዊ ሁኔታ ግምገማ በዚህ ደረጃ ያከናወኑትን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ፣ የክልል ቢሮዎችንና ቴክኒካል ቡድኑን ሚስተር ፋቢዎ አመስግነዋል።
በተለያዩ የዘርፉ ሙያተኞች በቀረቡ የነባራዊ ሁኔታ ግምገማ ሪፖርቶች ላይ ሰፊ ውይይት እየተደረገ ነው።