አውደ ርዕዩ የውሃና ኢነርጂ ዘርፉን ለማዘመን እየተሰራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።

አውደ ርዕዩ የውሃና ኢነርጂ ዘርፉን ለማዘመን እየተሰራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።   ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተዘጋጀው 2ኛው የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት ለጎብኚዎች ክፍት የሆነው አውደ ርዕይ የውሃና ኢነርጂ ዘርፉን ለማዘመን እየተሰራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ ከ "ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ" አቶ መላኩ ታፈሰ ገልፀዋል።   "ውሃና ንፁህ ኢነርጂ ለዘላቂ ዕድገት" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት የውሃና የኢነርጂ ዘርፉን ለማዘመን የሚሰሩ ስራዎችንም ለማስተዋወቅ ዕድል ፈጥሮልናል ያሉት አቶ መላኩ የከርሰምድር ውሃ ካርታ /ground water mapping/ ላይ የሚሰራው SUN WASH ፕሮጀክት ከዴንማርክ ያስገባውን titan machine የጂኦ-ፊዚክስ መሳሪያን በመጠቀም በጋምቤላ ክልል 8 መለስተኛ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ተሰርቶ ውጤታማ በመሆኑ ለሌሎች አጋር ድርጅቶች ለማስተዋወቅ ዕድል ፈጥሮልናል ብለዋል።   በመድረኩም በSUN WASH ፕሮጀክት በጋምቤላ ክልል የተሰራውን ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ተሞክሮም ለዕይታ ቀርቧል። ብዙ መዋዕለ ንዋይ ፈሶበት የሚቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶች ከተቆፈሩ በኋላ በቂ ወይም ምንም ውሃ ባለመኖሩ ውጤታማ ስለማይሆኑ ይህ ዘመናዊ መሳሪያ ግን የሚቆፈረው ጉድጓድ ውሃ መኖሩንና አለመኖሩን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።   ከዴንማርክ መንግስት በተገኘው ድጋፍ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮን ውጤታማ የሚያደርገውን ማሽን ኢትዮጵያ ውስጥ መጠቀማችን ለጉድጓድ ቁፋሮ የሚወጣውን ወጪ የሚቀንስና ዘመናዊ መሳሪያ በመሆኑ ለሌሎች አጋር ድርጅቶች ለማስተዋወቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው አክለዋል።   አቶ መላኩ አያይዘውም በመዲናችን ደረቅ ቆሻሻን በመጠቀም የሚሰራው ከሰል ጭሱን በማስወገድ የምንጠቀምበትን የከሰል ምድጃን የሚያመርተው ፕሮጀክት የአየር ብክለትን ለመቀነስ ከፍተኛ አሰተዋጽኦ የሚያደርገውን የተሻሻሉ ምድጃዎችን የሚያመርቱ የግል ድርጅቶችንም እናስተዋውቅበታለን ብለዋል።

Share this Post