የውሃ ሀብቶቻችን በዘላቂነት ለመጠቀምና ለማስተዳር ውይይት ትብብርና የጋራ እርምጃ ያስፈልጋል ተባለ፡፡
ጥቅምት 19/201ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ በሚገኘው እና ሶስተኛ ቀኑን ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት በውሃ ሀብት ዘርፍ በተገኙ ስኬቶች፣ መሻሻል ስሚገባቸውና የቀጣይ ርምጃዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡
የእለቱን መርሃ ግር አስመለክቶ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ውሃ የህልውናችንና የኢኮኖሚያችን መሰረት አሁን ላይ ደግሞ ለብልጽግና ፣ ለሰላምና ለልማት ወሳኝ የሆነ ስትራቴጂካዊ ሀብት ሆኖ ብቅ ማለቱን ጠቅሰው ሆኖም ግን በጣም ተጋላጭ ፣ አከራካሪ እና አለም አቀፍ ስጋቶችም ሁሉ በውሃ ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ለዘላቂ ልማትና ለሰብዓዊ ደህንነት ማእከላዊ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ይህ ዓለም አቀፍ እውነታ ውድ የሆነውን የውሃ ሀብቶቻችን ለማስተዳር፣ ደህንነቱን ለመጠበቅ ፣ ለመምራትና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ውይይት ፣ትብብርና የጋራ እርምጃ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ክቡር አቶ ሞቱማ ገለጻ ዛሬ የምናደርገው ውይይት እያንዳንዱ ዜጋ ደህንነቱ የተጠበቀ ውሃ ማግኘት እንዲችል ፣ወንዞቻችን ፣ሀይቆችችን እና እርጥበታማ መሬቶቻችን ሁሉ ደህንነታቸው ተጠብቆ ዘላቂነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ እና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ ርምጃ የምንወስድበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡
ውሃ አላቂ ሀብት ነው ያሉት ክቡር አማካሪው ይህንን አላቂ ሀብት ህይወቱን ጠብቆ ለማቆየት ብሎም ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ መንከነባከብ እና በጥበብ መምራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
እንደሀገር የውሃ ፣ ሳኒቴሽንና ሀይጅን አገልሎቱን ተደራሽ በማድረግ ፣የውሃ ሀብት ልማትን በማስፋፋትና የውሃ ሀብት አስተዳደርን በማጠናከር ረገድ አስደናቂ እድገት አሳይታለች ያሉት አማካሪው በተፋሰስ ልማት አስተዳር ፣በሀይድሮሜትሮሎጂ የመረጃ ስርዓት እና በአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ፕሮግራሞች ላይ ያሳየችው ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ሆኖም ግን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ፣ፈጣን የከተሞች መስፋፋት ፣ የኢንዱስትሪ እድገትና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት በውሃ ጥራትና ብዛት እንዲሁም ሳኒቴሽንና ሀይጅን አገልሎት አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን አክለው ገልጸዋል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሳምንት "ውሃና ንጹህ ኢነርጂ ለዘላቂ እድገት" በሚል መሪ ቃል የሚከበርበት ዋና ዓላማ ውሃ የቴክኒክ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ ፣ አካባቢያዊና ፖለቲካዊ ግዴታ መሆኑንም አውቀን እንደሀገር የውሃ ፣የኢነርጂ ፣የአካባቢና የስነምህዳር ፣የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር አቀራረቦችን ማጠናከር አለብን ብለዋል፡፡
አክለውም የውሃ ሀብትን መልሶ ጥቅም ላይ እዲውል በተፈጥሮ ላይ መሰረት ያደረጉ መፍሄዎችን፣ የፈጠራ እውቀቶችን እና ልምዶች ማዳበር እንደሚገባ፣ የመሬት አስተዳደር ሁሉን አቀፍ ፣ግልጽ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን ለማረጋገጥ መንግስት የአካባው ማህበረተሰብ ፣የግሉ ዘርፍ እና አካዳሚክስ መከላከል ያለው አጋርነት መጎልበት እንዳለበትና በውሃ አስተዳደርና በዋሽ አገልሎቶች ውስጥ ምርጥ ልምዶችን ለመቀመር አጋርነትና ትብብርን ማጠናር እንደሚገባ ክቡር አቶ ሞቱማ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡