የአዴሌ ፕሮጀክት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲያካሄድ የነበረው የውይይት መድረክ ለቀጣይ ስራ የጋራ ግንዛቤ ያስጨበጠና ቅንጅታዊ አሰራርን የሚፈጥር ነው ተባለ።
ጥቅምት15/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ለሁለት ቀናት በአዋሽ ሰባት ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲካሄድ የነበረው የአዴሌ ፕሮጀክት የውይይት መድረክ ለቀጣይ ስራ የጋራ ግንዛቤ ያስጨበጠና ቅንጅታዊ አሰራርን የሚፈጥር ነው ሲሉ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በውይይቱ ማጠቃለያ ሊይ ተናግረዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ሀሳብ አስተያየቶች በተለይ በኢነርጅ አደረጃጀት ጋር በተያያዘ ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማያያዝ ምላሽ ሰጥተዋል።
የተጀመረውን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክሮ መቀጠል አዋጭነት እንዳለው በመግለጽ ያሉብንን የአቅም ውስንነቶች መቅረፍ እንደሚገባና ከውይይቱ የተገኘውን ግብዓት በመውሰድ አተገባበር ላይ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን በመሙላት ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚጠበቅም አሳስበዋል።
በቀጣይም ተግባር ተኮር የአቅም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና ከሶላር ጋር በተያያዘ ለሚሰሩ ስራዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ጨምረው ገልጸዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአደሌ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አዲስአለም መብራህቱ ፕሮጀክቱ በዋናነት የክልሎችና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን የሚጠይቅና የሚተገበር መሆኑን አውስተው፤ ስልጠናውም በአደሌ ፕሮጀክት የአካባቢና ማሕበራዊ አስተዳደር መተግበሪያ ሰነዶች ላይ ሰፊ ትኩረት በማድረግ እንደተሠጠ አብራርተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጀንደር ስፔሻሊስ የሆኑት ወ/ሮ አምሳሉ ሁንዴ የአደሌ ፕሮጀክት ከስርዓተ ጾታ ጋር በተለይ ለሴቶች ዘመናዊ ኢነርጂን ተደራሽ በማድረግ ያለባቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና የጤና ችግሮችን ለመፍታት በሚሠጠው ጠቀሜታ ላይ ገለጻ አድርገዋል።