የመቀሌ ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ፣ማጣሪያና ማስወገጃ የኦፕሬሽንና ጥገና ፕሮጀክት ግንባታ ውል ስምምነት ተደረገ።

የመቀሌ ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ፣ማጣሪያና ማስወገጃ የኦፕሬሽንና ጥገና ፕሮጀክት ግንባታ ውል ስምምነት ተደረገ። ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመቀሌ ከተማን የፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ማጣሪያና ማስወገጃ የኦፕሬሽንና ጥገና ፕሮጀክት ግንባታ ከአሰር ኮንስትራክሽን ኃ/የተ/የግ/ማህበር ጋር የውል ስምምነት አደረገ። ስምምነቱን የፈረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የአሰር ኮንስትራክሽን ብዙ ልምድ እንዳለው አስታውሰው፤ የመቀሌን ህዝብ በሚሰራው ስራ ተጠቃሚ ለማድረግ የተቻላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም ከመቀሌ ከተማ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ጽ/ቤት ጋር በጋራ ሆነው የሚመለከታቸውንም በማሳተፍ የመቀሌ ህዝብ ችግር በፍጥነት ተፈቶ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የተቻላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል። በትግራይ ክልል የመቀሌ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አሸናፊ ዘአብርሃ በኛ በኩል የሚሰጠንን አቅጣጫ ተቀብለን በክልሉም ሆነ በከተማው ጥሩ ስራ ሰርተን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እናደርጋለን ብለዋል። የአሰር ኮንስትራክሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ የማነ አብርሃ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ትላልቅ የውሃ ፕሮጀክቶች ላይ መሳተፋቸውን አስታውሰው የከተማ አስተዳደሩ ካገዛቸው በፍጥነትና በጥራት ሰርተው እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል። የሁለተኛ ከተሞች መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ቴክኒካል አማካሪ አቶ ነጋሽ አዱኛ በአስቸኳይ ወደ ተግባር እንዲለወጥና አገልግሎት እንዲሰጥ የክቡር ሚኒስትሩ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን አስገንዝበዋል፡፡ አክለውም አቶ ነጋሽ የመቀሌ ከተማ ህዝብ ከአንድ ሚሊዮን በላይ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ተሰርቶ ተጠቃሚ እንደምታደርጉ እናምናለን ብለዋል። ግንባታና ጥገናው በብር 397,299,678.22 እና በዶላር 12282 324.06 ከአለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ የሚከናወን ሲሆን በውሉ መሰረት በ18 ወራት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

Share this Post