ለማንኛውም ልማት ወሳኝ የሆነ የውሃ ሀብትን በሚገባ አውቀን በአግባቡና በቁጠባ መጠቀም እንደሚገባ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ አሳሰቡ።

ለማንኛውም ልማት ወሳኝ የሆነ የውሃ ሀብትን በሚገባ አውቀን በአግባቡና በቁጠባ መጠቀም እንደሚገባ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ አሳሰቡ። አዳማ: ጥቅምት 7/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአዋሽ ተፋሰስ የውሃ ምደባ እቅድን ከባለድርሻ አካላት ጋር እየገመገመ ነው። የውሃ ሀብት ለማንኛውም ልማት መሠረት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር ጥንቃቄ ልናደርግበትና በቁጠባ ልንጠቀም እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ በመክፈቻ ንግግራቸው አሳስበዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመራቸው የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን እንዲሁም ፣የኢነርጂ ልማት ዘርፎች አንዱ እና ለሁሉም ልማት ወሳኝ በሆነው የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቀሱት ክቡር አቶ ሞቱማ የውሃ ሀብቱን በሚገባ አውቀን ካልተገበርነው ሁሉም ልማት ችግር ውስጥ ይገባል ብለዋል። የውሃ ሀብታችን የት እንደሚገኝ በመጠን ፣ በጥራት ፣ ለምን አገልግሎት እንደሚውል ፣ እንዴት እንደምንጠቀምና በምን አይነት መልኩ መጠቀም እንደሚገባን ጭምር በሚገባ በማወቅ አላቂ ሀብት የሆነውን ውሃ በቁጠባ መጠቀም ይገባል ብለዋል። አሁን ላይ ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የውሃ ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ ውሃ ላይ የሚኖሩ ግጭቶችን ለመፍታት የውሃ ምደባ ስርዓቱን በሚገባ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባና ለዚህ ደግሞ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። የአዋሽ ተፋሰስ ከመነሻ እስከ መድረሻው በርካታ ጠቀሜታዎችን እያበረከተ ነው ያሉት ክቡር አቶ ሞቱማ ይህንን ሀብት በሚገባ አውቀነው ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ በፍትሃዊነት እና የውሃ ዋጋ ገብቶን ልንጠቀምበት ይገባልም ብለዋል። የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደን አብዶ የአዋሽ ተፋሰስ በተፋሰሱ ውስጥ በፍቃድ ላይ የተመሰረተ ፍታሃዊ፣ ዘለቄታዊነት ያለው፣ አሳታፊና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የውሃ ሀብት ምደባን ተግባራዊ ለማድረግ ላለፉት 4 ዓመታት ከብሉ ዲል አዋሽ ጋር በመተባበር በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የበጀት ዓመቱን የውሃ ምደባ ከፍ ባለ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም በላይኛው አዋሽ ላይ የተገኙትን ልምዶች ወደ መካከለኛው እና ታችኛው አዋሽ ለማስፋት የሁሉም አካባቢ ተጠቃሚዎችን ያሳተፈ መድረክ ተዘጋጅቷል ብለዋል። በቀጣይም የተጠቃሚዎችን የውሃ ፍላጎት የማሰባሰብ ፣ የማደራጀት፣ የውሃ ምደባውን ሰነድ በጋራ የማዘጋጀት፣ የማጸደቅና በጋራ ትግበራውን የመከታተል ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ በትግበራ ሂደቱ ውስጥ የተፋሰሱ የውሃ ተጠቃሚዎች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉም ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በመድረኩ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማስፈን በባዘርኔት ፕሮጀክት እየተተገበሩ ያሉ ፣ የአዋሽ ተፋሰስ የውሃ መድባ ሂደት፣ የ2017 የውሃ ምደባ የመስክ ምልከታ ሪፖርት፣ በላይኛው አዋሽ ላይ የተሰሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በውሃ ተጠቃሚዎች ምዝገባ፣ ፍቃድ እና ክፍያ ስርዓት ላይ ያመጣው ውጤት ቀርቦ ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡ መድረኩ በብልዲል እና ባዘርኔት የቴክኒክና የፋይናንስ ትብብር የተዘጋጀ ሲሆን የውሃ ምደባ ቴክኒካል ኮሚቴ፣ የውሃ ምደባ ክትትል፣ግምገማና ትምህርት ቡድን፣ ከፍተኛ የውሃ ተጠቃሚዎች፣ የመስኖ ተጠቃሚ ማህበራት እና የዘርፉ ሙያተኞች እየተሳተፉ ነው። ውይይቱ በነገው እለትም የሚቀጥል ይሆናል።

Share this Post