በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ኩልፎ ወንዝ ዙሪያ ለሚሰራው የጎርፍ መከላከል ተግባር የዓለም ባንክ ልዑካን ቡድን የመስክ ምልከታ አካሄደ

በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ኩልፎ ወንዝ ዙሪያ ለሚሰራው የጎርፍ መከላከል ተግባር የዓለም ባንክ ልዑካን ቡድን የመስክ ምልከታ አካሄደ መስከረም 21/ 2018 ዓ.ም (ዉ.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጄክት ከሚተገበሩት መካከል በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ኩልፎ ወንዝ ላይ የሚሰራውን የጎርፍ መከላከል ሂደት ለመመልከት የዓለም ባንክ ልዑካን ቡድን የመስክ ምልከታ አካሄደ። የፕሮጄክቱን አፈጻጸም አስመልክቶ የፕሮጄክቱ ቴክኒካል ቡድን መሪ አማካሪ ኢንጅነር ቴዎድሮስ ወርቁ አስቀድመው ገለጻ አቅርበዋል። ገለጻውን አስመልክቶ በቀረቡ ማብራሪያዎች ዙሪያ ተሳታፊዎቹ ገንቢ አስተያየቶች የሰነዘሩ ሲሆን በቀጣይ በፕሮጄክቱ ሂደት ለሚኖረው ትግበራ አዎንታዊ ግብዓት እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል። በተያያዘም የፕሮጄክቱን ወቅታዊ አፈጻጸም ለመመልከት የመስክ ምልከታ ተካሂዷል። በምልከታው ወቅትም በፕሮጄክቱ የቴክኒካል ስራዎች፣ አከባቢያዊና ማህበራዊ ተጽዕኖን ከማረጋገጥ አንጻር የተከናወኑ ተግባራት እንዲሁም ከዕቅዱ አንጻር የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ የዓለም ባንክ ልዑክ ቡድን መሪ ሱራብ ዳኒ (Surab Dani) የማሻሻያ ሀሳቦችን አንስተዋል። አክለዉም የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጄክት አስተባባሪ አቶ ተመስገን ከተማ ተጨማሪ ማብራሪያ በመስጠት በቀጣይ በሚኖረው አፈጻጸም ተግባራዊ ለማድረግ እንደግብዓት እንጠቀምበታለን ሲሉ አስተያየታቸውን ለግሰዋል። በቀጣይ በሚኖሩት ቀናትም ከወረዳው አስተዳደርና ከማህበረሰቡ ጋር ለመምከርና የአርባምንጭ የአየር ንብረት ጣቢያን ለመጎብኘት ዕቅድ መያዙ ተመልክቷል። በመስክ ጉብኝቱ ወቅት የዓለም ባንክ ልዑካን፣ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጄክት ባለሞያዎች፣ የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባና ሌሎች የፕሮጀክቱ ተቋራጮችና አማካሪዎች ተሳትፈዋል።

Share this Post