የኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ የተሻለና የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል ሪፎርም እንደሚያስፈልገው ተገለጸ ፡፡
መስከረም 20/2018 ዓ/ም (ውኢሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ደረጃ ከተውጣጡና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር የኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ የተሻለና የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል ሪፎርም ለማድረግ ምክክር ተደረገ፡፡
የምክክር መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ የኢትዮጵያ የኢነርጂ ዘርፍ የተሻለና የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል ሪፎርም እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሪፎርሙን ተከትሎ ባለፉት 4 አመታት በኢነርጂው ዘርፍ ብዙ ስራዎች ተሰርተው ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበችና ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የኤሌክትሪክ ሀይል እያቀረበች እንደሆነና በቀጣይ ለሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ተደራሽ ለማድረግ በአፍሪካ የኢነርጂ ሀብት /ቋት/ ለመሆን እየሰራች ነው ብለዋል።
አያይዘውም እንደ ሀገር ከፍተኛ ታዳሽ ኢነርጂ ሀብት ቢኖርም በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው የዚህም ማሳያ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የፋይናንስ ቁመናቸው በመንግስት ድጋፍ እና ድጎማ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ፣ የአገልግሎት አሰጣጣቸውም በሚጠበቀው የጥራት፣ ብቃትና ዘመናዊነት ልክ ባለመሆኑ ሪፎርሙ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል ፡፡
እንደ ሀገር የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቀሚ 54 በመቶ የህብረተሰብ ክፍል ብቻ እንደሆነና የንጹህ ማብሰያ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚው የህብረተሰብ ክፍልም10 በመቶ የበለጠ እንዳልሆነ ቀሪዉ 90 በመቶ የህብረተሰብ ክፍል ለምግብ ማብሰያነት ባዮማስ (የእንጨት ማገዶ) እንደሚጠቀሙ እና ይህም የአየር ንብረት ብክለትንና የአፈር መሸርሸርን ከማስከተሉም ባሻገር በህጻናትና ሴቶች ጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመመከት የኢነርጂው ዘርፍ ሪፎርም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በመድረኩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስራስኪያጆችና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች የአሁናዊ የኢነርጂ ዘርፍ ቁመና ምን እንደሚመስል ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጎ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የግሉ ሴክተርና የአጋር ድርጅት ተወካዮች ጥያቄዎችን አንስተው ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በውይይት መድረኩ የአሜሪካ ፣የአውሮፓ፣የአፍሪካ ሀገራት አጋር ድርጅቶች፣ጂአይ ዜድ፣የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የዓለም ባንክ እና ሌሎችም በርካታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ድርጅቶች፣ ግለሰቦች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡