አስተማማኝ ፣ አዋጭ እና ዘመናዊ ኢነርጂ ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሆኑን ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ገለጹ።

አስተማማኝ ፣ አዋጭ እና ዘመናዊ ኢነርጂ ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሆኑን ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ገለጹ። ሚያዚያ 26/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብርሃን ተደራሽነት ለሁሉም (የአዴሌ) ፕሮጀክት አፈጻጸምን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየገመገመ ነው። በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ አስተማማኝ ፣ አዋጭ እና ዘመናዊ ኢነርጂ ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። ያለ ኢነርጂ ዘላቂ የሆነ ልማትና እድገት እንዲሁም ብልጽግና ሊረጋገጥ አይችልም ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የለውጡ መንግስት ይህንን በመረዳት ለዘርፉ የሠጠው ትኩረት ከፍተኛ ነው ብለዋል። እንደ ሀገር እያደገ ለመጣው ኢኮኖሚ የሚመጥን ኢነርጂ ለማቅረብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል። 150ጌጋ ዋት ታዳሽ ኢነርጂ እንደ ሀገር ቢኖርም ጥቅም ላይ የዋለው ግን በጣም ውስን በመሆኑ 54 በመቶ ብቻ ህዝባችን የሀይል ተጠቃሚ ተደርጓል ብለዋል። የንጹህ ኢነርጂ ተጠቃሚ የህብረተሰብ ክፍልም ከ10 በመቶ የሚበልጥ አለመሆኑንም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለው ገልጸዋል። ይህንን ችግር በመቅረፍ እስካሁን የሀይል ተደራሽ ያልሆኑ 57 በመቶ ኢትዮጵያውያንን ችግር ለመቅረፍ ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል። በፕሮግራሙም 65 በመቶ ህዝባችን ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ፣ከዋናው ኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙትን ደግሞ በሶላር ሚኒግሪድና በሶላር ሆም ሲስተም ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል። ለፕሮግራሙ ተግባራዊነትም የግሉን ዘርፍ በሀይል ማመንጨትና ማስተላለፉ ላይ ተሳታፊ ለማድረግ የኢነርጂ ፖሊሲ በመከለስ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል። የመድረኩ ዋና አላማም ወደ ትግበራ ከገባ ሁለት አመት የሆነው የአዴሌ ፕሮጀክትን በሚገባ በመገምገም ተግዳሮቶቹን በመቅረፍ ከእስካሁኑ የተሻለ ስራ ለመስራት በመሆኑ በውይይቱ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። የሲዳማ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ኢ/ር ከበደ ጋኖሌ ክልሉ በአዴሌና በገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ተጠቃሚ ሆኗል ብለዋል። የኢነርጂ ጉዳይ እንደ ክልል ፖለቲካዊ ትርጉም ተሰጥቶት እየተሠራ ነው ያሉት የቢሮ ሀላፊው በአማራጭ ኢነርጂ ዘርፍ በ15 ወረዳዎች በ32 መንደሮች ንጹህ የማብሰል ዘዴን እንዲጠቀሙ ሰፊ ርብርብ እያደረግን ነው ብለዋል። እንደ ክልልም የባዮ ጋዝ መንደር ለመፍጠር እና የሶላር ሆም ሲስተምን ተግባራዊ ለማድረግ በጀት ተመድቦ እየተሰራ ነው ብለዋል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽን መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ዳቢ በፕሮጀክቱ ትግበራ ሂደት ተሳታፊ የሆኑ የክልልና የወረዳ ተወካዮች የክትትልና ግምገማ ስርዓት በማበጀት የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር መድረኩ ወሳኝ ነው ብለዋል። የአዴሌ ፕሮጀክት በተሻለ ፍጥነትና ጥራት እንዲተገበር ፣ ሁሉም የድርሻውን ለመውሰድ ፣ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ብሎም ልምድ ለመለዋወጥ መድረኩ ወሳኝ ነው ብለዋል። በመድረኩ የኦሮሚያ ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የማእከላዊ ኢትዮጵያና የሲዳማ ክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊዎች ፣ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ የፕሮጀክቱ ተወካዮች እና የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው።

Share this Post