ሁለተኛው አድዋችን የሆነው ህዳሴያችን የጋራ ማንነታችን መገለጫ ነው። ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ

ሁለተኛው አድዋችን የሆነው ህዳሴያችን የጋራ ማንነታችን መገለጫ ነው። ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የካቲት 21/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) 129ኛው የዓድዋ ድል በዓል “አድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል!” በሚል መሪ ቃል በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና ሰራተኞች ተከበረ። በአሉን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ሁለተኛው አድዋችን የሆነው ህዳሴያችን የጋራ ማንነታችን መገለጫ ነው፤ አድዋ የትም ቦታ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚዘክረው በመሆኑ ማንነታችንን ያበሰርንበት ነው ብለዋል። ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር በዘመቱበት ወቅት ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት ዘርፍ የድርሻቸውን በመወጣት አሻራቸውን ያኖሩበትና ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት በመሆኑ ልንዘክረው ይገባል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ጀግኖች አባቶቻችን በሀገር ጉዳይ በጋራ ሲቆሙ ብሔር ሳይለዩ የጀግንነት ድርሻቸውን ተወጥተዋል ብለዋል። ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም ሁለተኛው አድዋችን የምንኮራበትና የአንድነታችን የጋራ መገለጫችን በመሆኑ በወቅቱ የነበሩ መሪዎች ዋጋ ከፍለው እዚ አድርሰውልናልና ልናስቀጥለው ይገባል፤ በተጨማሪም የይቻላል መንፈስ ያዳበርንበት በመሆኑ የጋራ ሀገር ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የምትሆን ኢትዮጵያን እንገምባ ብለዋል። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌትነት ጌጡ በዓሉን አስመልክቶ የተዘጋጀውን የመወያያ ሰነድ አቅርበው እንደተቋም ሁለተኛውን አድዋችንን ለማስቀጠል ሁሉም በተሰማራበት ዘርፍ ኃላፊነታችንን በመወጣት የራሳችንን አሻራ ማስቀመጥ እንዳለብን ጠቁመዋል። መድረኩ በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር የተጀመረ ሲሆን በቀረበው የመወያያ ሰነድ ዙሪያ ከሰራተኞች በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ክቡር ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

Share this Post