በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን ወልመራ ወረዳ ብርኩሳሜ ቀበሌ ጋቢ ሮቢ ሞዴል የባዮ ጋዝ ዳይጀስተር መንደር ተመረቀ፡፡
ግንቦት 15/2015ዓም ( ው.ኢ.ሚ.) በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል፣ ምእራብ ሸዋ ዞን ወልመራ ወረዳ ብርኩሳሜ ቀበሌ ጋቢ ሮቢ መንደር በኔዘርላንድስ የልማት ድርጅት (SNV) እና በመንግስት ድጋፍ የተሰራው ሞዴል የባዮ ጋዝ ዳይጀስተር መንደር ተመረቀ፡፡
የጋቢ ሮቢ ሞዴል የባዮጋዝ መንደር 154 የሚጠጉ አባዎራዎች ያሉበት መሆኑንና የ72 አባወራዎች ዳይጀስተሮች ቴክኒካል ብቃት ያሟሉ ባዮዳይጀስተሮች ናቸው ያሉት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ መንደሩ በባዮጋዝ ፕሮግራም በክልሉ ለ2ኛ ጊዜ የተመረቀ መንደር ነው ብለዋል፡፡
አስተዳዳሪው በማከል የባዮጋዝ ፕሮግራም በኦሮሚያ ክልል፤ የሀይል አቅርቦት በሌለባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ረጅም ጌዜ ማስቆጠሩን አውስተው፤ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ መጠቀም ለህብረተሰቡ ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባሻግር ለአካባቢ ጥበቃ እና ለግብርና ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ገልጸው ይህን ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ በጣም ቀላልና ወጪ ቆጣቢ ነው ብለዋል፡፡
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሄራዊ ባዮጋዝ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተመስገን ተፈራ በበኩላቸው ፕሮግራሙ በ2030 ዓ.ም. 165 ሺ የሚደርሱ አባዎራዎችን የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ በኔዘርላንድስ የልማት ድርጅት (SNV) እና ከመንግስት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ገልጸው የባዮጋዝ ፕሮግራም ከሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጤናና ማህራዊ ጫናን ለመቀነስ ብሎም የአየር ንብረትን ለመጠበቅ ይረዳ ዘንድ ንጹህ ኢነርጂን ለማዳረስ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ አያይዘውም የተመረቀው ሞዴል መንደር ላይ 72 አባዎራዎች የባዮጋዝ ተጠቃሚ ከመሆን አልፈው ባዮ ሳላሪን እና ተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም የእንስሳት መኖ በማምረት ለመሸጥ እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡
የብሔራዊ ባዮጋዝ ማስፋፋፊያ ፕሮግራም በአውሮፓ ህብረት (EU) እና በመንግስት የገንዘብ ድጋፍ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በኢትዮጵያ 8 ክልሎች ተግባዊ በመደረግ ላይ ነው፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የኔዘርላንድስ የልማት ድርጅት (SNV) ካንትሪ ዳይሬክተር፣ የምእራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ሀላፊና ሌሎች እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡