የሶላር ኢነርጂን በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ አማራጭ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የሶላር ኢነርጂን በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ አማራጭ መሆኑ ተገለጸ፡፡ መጋቢት/2015ዓ.ም(ውኢሚ) ከዋናው ኤሌክትሪክ መስመር ውጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ የሶላር ኢነርጂን በመጠቀም የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ አማራጭ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር/ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ከሰሞኑ በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በተለያዩ ቀበሌዎች በመዘዋወር ምርታማነትን ለመጨመር እየተተገበረ ያለውን የሶላር ማቀዝቀዣ የሙከራ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በጉብኝታቸው ወቅት በሰጡት ቃለመጠይቅ የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ዋና ዓላማ ለማህበረሰቡ የመብራት አገልግሎት ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ለማብሰያነትና ለግብርና ምርታማነትም ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከ GIZ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በክልሉ አራት ወረዳዎች ለተደራጁ አምስት የህብረት ስራ ማህበራት አትክልትና ፍራፍሬዎችን ለገበያ እስኪያቀርቡ ድረስ ሳይበላሹ እንዲቆዩ ለማድረግ የሚያስችሉ አምስት የሶላር ማቀዝቀዣዎች ተተክለውላቸው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ የሲዳማ ክልል በፍራፍሬ ምርት የተሻለ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴታው ምርቱ ተሰብስቦ ወደ ገበያ እስኪደርስ ድረስ በምርቱ ላይ የሚደርሰው ጉዳት በመቀነስ በተለይም አርሶ አደሩ ምርቱን ለመሸጥ ገበያ ፍለጋ የሚንከራተትበትን ችግር የሚፈታና ህብረት ስራ ማህበራቱም ምርቱን በአንድ ላይ ሰብስበው ለተጠቃሚው እስከሚያደርሱ ባለው ጊዜ ሳይበላሽ የሚቆይበትን እድል የፈጠረ በመሆኑ ምርታማነትን ለመጨመርና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም የሶላር ማቀዝቀዣዎቹ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገባቸው ሲሆን አንዱ ማቀዝቀዣ እስከ 40 ኩንታል የመያዝ አቅም አለው ብለዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም በኦሮሚያና በአማራ ክልሎችም የተለያዩ የጥራጥሬ ምርቶችን በማድረቅ እስከ ዘር ድረስ ለማቆየት የሚያስችሉ የሶላር ማድረቂያዎች የሙከራ ትግበራ እየተደረገ መሆኑን እና ይህ የሙከራ ፕሮጀክት ጅማሮ የግል ባለሀብቶች፣ የተለያዩ ማህበራት እና መንግሰትም እንድሳተፉበት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ መስፍን መጩካ እንዳሉትም የህብረት ስራ ማህበራት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ከአርሶ አደሩ ሰብስበው ለይርጋለም አግሮ ፕሮሰሲግ ኢንዱስትሪ እስኪያቀርቡ ድረስ ምርታቸው ላይ የመበላሸት አደጋ እየደረሰ ተጠቃሚነታቸውን እየቀነሰባቸው እንደሆነ ጠቅሰው ለሀገራችን አዲስ የሆነውና በሶላር የሚሰራው ማቀዝቀዣ መተከሉ ለህብረት ስራ ማህበራቱ ምርቱን በአንድ ላይ ሰብስቦ ለማቅረብ እና አስኪጓጓዝ ባለው ጊዜ በምርቱ ላይ ጉዳት እንዳይደር በማድረግ ከወጭም ከጉልበትም አንጻር ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ለአርሶ አደሩም ገበያ ፍለጋ በማጓጓዝ የሚያጠፋውን ጊዜና ወጭ በመቆጠብ እንዲሁም በስፋት እንድያመርቱ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ምርትን ኤክስፖርት ለማድረግ ትልቅ አቅም ነው ሲሉም አክለዋል፡፡ ተዘዋውረን በጎበኘንባቸው ቀበሌዎች ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮችና የህብረት ስራ ማህበራት አባላትም ገበሬዎች ፍራፍሬዎችን በስፋት እያመረቱ ቢሆንም ከማሳው ተሰብስቦ ገበያ እስኪደርስ ድረስ ግማሽ የሚሆነው ምርት በመበላሸት እንደሚቀርና ተጠቃሚነታቸውም ያን ያክል እንደነበር አውስተው አሁን ላይ ይህ የማቀዝቀዣ ማሽን መተከሉ ምርቱ አስኪሸጥ ድረስ ሳይበላሽ ሲለሚቆይ ወደ ተጠቃሚው ለማድረስ ስራችንን አቅልሎልናል ተጠቃሚነታችንም በዚያው ልክ ይረጋገጣል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

Share this Post