በኢብሮ-ሰዴን ንዑስ ተፋሰስ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ክትትልና ድጋፍ ተደረገ

በኢብሮ-ሰዴን ንዑስ ተፋሰስ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ክትትልና ድጋፍ ተደረገ መስከረም 23/2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የBaSRINET ፕሮጀክት በዋቢ-ሸበሌ ተፋሰስ በምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን ባቢሌ ወረዳ ኢፋዲን ቀበሌ በሚገኘው ኢብሮ-ሰዴን ንዑስ ተፋሰስ እየተከናወኑ ያሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ የተፋሰስ ልማትና የኑሮ ማሻሻያ ሥራዎችን ክትትልና ድጋፍ አደረገ። የክትትልና ድጋፍ ቡድኑ በኩፋካሳ ንዑስ ቀበሌ የሚገኘውን የችግኝ ጣቢያ በመጎብኘት የችግኝ ልማትና ስርጭት ሂደትን ገምግሟል፤ ለቀጣዩ የልማት ዑደትም የቴክኒክ ድጋፍ ሰጥቷል። በተጨማሪም ቡድኑ የተፋሰስ ተጠቃሚዎች ማህበር (WUA) አባላት የሚያካሂዱትን የሚዞር ፈንድ እና የፍየል ማደለብና ማራባት ሥራ በመጎብኘት የተፋሰስ ልማት ከኑሮ ማሻሻያ ጋር ያለውን ትስስር አስመልክቶ ከማህበረሰቡ ጋር ተወያይቷል። በኢብሮ-ሰዴን ንዑስ ተፋሰስ የላይኛው ክፍልም በማህበረሰቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ እየተከናወኑ ያሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችንም ተመልክተዋል። ቡድኑም ከማህበረሰቡ ጋር በመስክ ሥራው ላይ በቀጥታ በመሳተፍ አበረታቷል። በተመሳሳይ ከባቢሌ ወረዳ አመራር እና ከግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊዎች ጋር በተደረገ የግብረመልስ ውይይት የታዩ ችግሮችና ተጨማሪ ድጋፍ የሚፈልጉ ጉዳዮችም በውይይቱ ተነስተው፤ በተለይም የቴክኒክና ግብዓት ድጋፍ፣ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር፣ የችግኝ ጣቢያ ማሻሻያና የውሃ አቅርቦት ሥራዎች እንዲጠናከሩ አቅጣጫ ተሰጥቷል። በመጨረሻም ቡድኑ በጅግጅጋ የሚገኘውን የዋቢ-ሸበሌ ተፋሰስ BaSRINET የተፋሰስ ትግበራ ክፍል (BIU) ፅህፈት ቤት በመጎብኘት የሥራ አፈፃፀሙንም ገምግሞ፤ የተፋሰስ ልማት ዕቅዱ በተቀናጀ መልኩ እንዲፈጸም፣ የክትትልና ሪፖርት ስርዓቱም እንዲጠናከር አቅጣጫ ተሰጥቷል። የክትትልና ድጋፍ ተልዕኮው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርንና የBaSRINET ፕሮጀክትን ባካተተ ቡድን ተመርቷል። የተቋሙን ተጨማሪ መረጃዎች ለማግኘት:- ፌስቡክ https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/ ቴሌግራም http://t.me/mowieethiopia ዌብሳይት http://mowe.gov.et X/ትዊተር https://x.com/mowe_ethiopia ዩቱዩብ https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s ቲክቶክ tiktok.com/@mowetikto

Share this Post