የኢንፍራንዝ ንዑስ-ተፋሰስ የዳሰሳ ጥናት እና የተቀናጀ የተፋሰስ ዕቅድ ዓውደ-ጥናት እየተካሄደ ነው።
የኢንፍራንዝ ንዑስ-ተፋሰስ የዳሰሳ ጥናት እና የተቀናጀ የተፋሰስ ዕቅድ ዓውደ-ጥናት እየተካሄደ ነው።
ባህርዳር፡-ታህሳስ 13/2018 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በብራይት /BRIGHT/ ፕሮጀክት የሚተገበር በአባይ ተፋሰስ የኢንፍራንዝ ንዑስ-ተፋሰስ የዳሰሳ ጥናት እና የተቀናጀ የተፋሰስ ዕቅድ የባለድርሻ አካላት የግምገማ ዐውደ-ጥናት እየተካሄደ ነው።
መርሃግብሩን በንግግር ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የክቡር ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ሚካኤል መሀሪ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአሁኑ ወቅት በውሃ አስተዳደር ዘርፍ፣ በኢነርጂ ዘርፍና በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሰፊ ስራ በመስራት ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አንስተው የዕለቱ ዓውደ-ጥናት ቀጣይ በተፋሰሶች ላይ በተለይ በኢንፍራንዝ ንዑስ ተፋሰስ ላይና መሬትንና የውሃ አካላትን ማዕከል ተደርጎ ለሚሰራ ስራና ለሚመዘገብ ውጤት ከፍተኛ እገዛ እነደሚያደርግ ተናግረዋል።
ዶ/ር ሚካኤል አክለው ፕሮጀክቱ ውሃንና መሬትን ማዕከል አድርጎ ከፌዴራል እና ከክልል የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ኤምባሲዎች ጋር የሚሰራ መሆኑን ገልፀው፤ ለተግባራዊነቱና ለውጤታማነቱ የሁሉም ባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራርና ትብብር ይጠይቃል ብለዋል።
ከፍተኛ አማካሪው የኔዘርላንድ ኤምባሲን በኢትዮጵያ እና ሌሎችንም አጋር ድርጅቶች ለልማት ስራ እያደረጉ ላለው የገንዘብ ድጋፍና ቀና አመለካከት ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበው ለስራው ተግባራዊነትና ውጤታማነት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የውሃና የኢነርጂ ፖሊሲ በመከለስ የበኩሉን ሁሉ እየተወጣና ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ እንዳለ አብራርተዋል።
በኔዘርላንድ ኤምባሲ በኢትዮጵያ የውሃ የመጀመሪያ ሴክሬታሪ ሊሶን ሬስጋድኡዋት /First secretary water M's Lison Rsgdeuaate/ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በዚህ ከፍተኛ ውጤት በሚያስገኝ የልማት ስራ ለመሳተፍ ዕድል በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን አንስተው ወደፊትም በሌሎች የልማት ስራዎች አብረው ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
M's Lison አክለውም መሬትንና የውሃ አካላትን ማዕከል ተደርጎ የሚሰሩ ስራዎች የህብረተሰቡን ህይወት በከፍተኛ ሁኔታ የመለወጥ አቅም ስላለው መንግስትና የግሉ ሴክተር በመደማመጥ፣ በመተባበርና ትኩረት በመስጠት መስራት ይገባል ብለው በፕሮጀክቱ ውስጥ ያሉትን መልካም አጋጣሚዎችንና ዕድሎችን አሟጦ ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ በውይይቱ ወቅት መነሳት አለበትም ብለዋል።
በመርሃ-ግብሩ የኢንፍራንዝ ንዑስ ተፋሰስ /Infranze Catchment/ ከስነ-ምህዳርና ከስነ-ህይወት አንፃር፣ ከአየር ንብረትና የውሃው ሁኔታ፣ ከውሃ ሀብት አስተዳዳር አንጻርና ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አንጻር አሁናዊ ተጨባጭ ሁኔታው ምን እንደሚመስል መረጃ ላይ የተደገፈ ሰነድ በዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ለውይይት ቀርቧል።
የግምገማ ዓውደ-ጥናቱ ቀጣይ ሁለት ቀናት እንደሚቀጥል፣ በውይይቶችና በግምገማ የጋራ መረዳት ላይ እንደሚደረስና የወደፊት የአሰራር አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ከመድረኩ ተገልጿል።
ስለተቋማችን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት
ፌስቡክ
https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/
ቴሌግራም
http://t.me/mowieethiopia
ዌብሳይት
http://mowe.gov.et
X/ትዊተር
https://x.com/mowe_ethiopia
ዩቱዩብ
https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s
ቲክቶክ
tiktok.com/@mowetikto