ከ 215 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጭ የ17 ፕሮጀክቶችን የመጠጥ ውሃ ጥናትና ዲዛን ከሚያከናውኑ አማካሪ ድርጅቶች ጋር የውል ስምምነት ተፈረመ፡፡
መስከረም 21/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት የሚተገበሩ የ17 ፕሮጀክቶችን የመጠጥ ውሃ ጥናትና ዲዛይን ከሚያከናውኑ አማካሪ ድርጅቶች ጋር ከ 215 ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጭ የውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱ የተፈረመው ከለልፍቱ አጠቃላይ የልማት አማካሪ ኃላ/የተ/የግ/ማህበር ፣ከአሀዱ ኢንጂነሪግ አማካሪ ኃላ/የተ/የግ/ማህበር ፣ ከሬድዋን ሀይድሮኢኮሎጂ ሶሉሽንስና ከኢትዮጵያ ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን ጋር ነው፡፡
ስምምነቱን የፈረሙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት ድርቅ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች አስቸኳይ መፍትሄ ለመስጠት 110 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በታቀደው መሰረት የ22 ፕሮጀክቶች ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዛሬው ስምምነትም የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰምድር ውሃ ፕሮጀክት አካል የሆነና በፕሮጀክቱ በሁለተኛው ዙር በደቡብ ኢትዮጵያ ፣በአፋር ፣በቤኒሻንጉል ጉምዝና በኦሮሚያ ክልሎች ለሚገነቡ 17 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የጥናትና ዲዛይን ስራ ለማከናወን ከአማካሪ ድርጅቶች ጋር የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
አማካሪ ድርጅቶቹ የተሟላ መሳሪያ እና የሰው ሀይል ቀድመው በማደራጀት ጥራቱን በጠበቀና የህብረተሰቡን ችግር ባማከለ መልኩ የግንባታ ስራው እንዲሰራና ህብረተሰባችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆን ውጤታማ ዶክመንት በማዘጋጀት የድርሻቸውን እንዲወጡ ያሳሰቡት ክቡር ሚኒስትር ዴታው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ለስራው ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደረግ ገልጸዋል፡፡
የአራቱም አማካሪ ድርጅት ተወካዮች የዚህ በጎ ተግባር ተካፋይ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ በገቡት ቃል መሰረት የተሰጣቸውን እድል በአግባቡ በመጠቀም ስራውን በጥራትና ከተቀመጠው ጊዜ ቀድመው በማጠናቀቅ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቻላቸውን ጥረት ሁሉ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡
የጥናትና ዲዛይን ስራው በአምስት ወር ተኩል ጊዜ እንደሚጠናቀቅም ነው በውል ስምምነቱ የተገለጸው፡፡