የአየር ንብረት ተፅዕኖን የሚቋቋም የውሃ ኢንቨስትመንት ዕቅድ ላይ ቀጠናዊ የስልጠና አውደጥናት እየተካሄደ ነው።
የአየር ንብረት ተፅዕኖን የሚቋቋም የውሃ ኢንቨስትመንት ዕቅድ ላይ ቀጠናዊ የስልጠና አውደጥናት እየተካሄደ ነው።
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 09/2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ጋር በጋራ ያዘጋጁት የአየር ንብረት ተፅዕኖን የሚቋቋም የውሃ ኢንቨስትመንት ዕቅድ ላይ ቀጠናዊ የስልጠና አውደጥናት በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ እና በሚኒስቴር መ/ቤቱ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የውሃ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም ፎካል ፐርሰን ዶክተር ምትኩ በድሩ መድረኩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በውሃው ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን መቋቋም እንዲችሉ ሆነው እንዲሰሩና ከተለመደው ኢንቨስትመንት በተጨማሪ ሌሎች ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ የሚያስችል የኢንቨስትመንት ፕሮግራም ለማዘጋጀት ያለመ ስልጠና ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ለአባል ሀገራት ተቋማዊ አቅምን ለማጠናከርና ለኢንቨስትመንት ብቁ የሆኑ የፕሮጀክቶች ዝግጅት ላይ ቴክኒካል የአቅም ግንባታን ለማጎልበት ያግዛልም ነው ያሉት።
ዶ/ር ምትኩ አክለውም በባንክ ሊደገፉ የሚችሉና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ሊቋቋም የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ዲዛይን ለሚደረግበት ስትራቴጂ ላይ የተሻለ ግንዛቤ በመፍጠር መንግስት ኢንቨስት ከሚያደርገው በተጨማሪ ለአየር ንብረት ለውጥ የተዘጋጁ ፋይናንሶችን ሀብት የማሰባሰብ ስልቶችን እንዴት እንደሚዘጋጅ፣ ምንምን መስፈርቶችን እንደሚፈልጉና ፋይናንሶቹ እነማን እንደሆኑ ለመለየትም የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ተወካይ ሚስተር ሐርሰን ንያምቤ በኮሚሽኑ ዘላቂ የአካባቢ እና የብሉ ኢኮኖሚ ዳይሬክተር በመድረኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ስልጠናው የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ ዘላቂ ፕሮጀክቶችን ማቀድና መተግበር፣ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት፣ ከልማት አጋሮችና ከግሉ ዘርፍ የሚገኙ ሀብቶችን ለማሰባሰብ አቅም መገንባት፣ የአፍሪካ አገራት ያላቸውን ልምድ፣ ዕውቀትና የቴክኖሎጂ አቅም በመጋራት የውሃ ችግሮችን በትብብር መፍታት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
ሚስተር ሐርሰን አያይዘውም ከመድረኩ የሚገኙ ዕውቀቶችንና ምክረ ሐሳቦችን ወደ ተግባር በመቀየር ፋይናንስ ሊገኝላቸው የሚችልና ውጤት የሚያመጡ ፕሮጀክቶችን መንደፍ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለአፍሪካ ህብረት ቴክኒካል ድጋፍ የሚሰጥ የከርሰምድር ውሃ አጋርነት /Groud water Partnership/፣ በኮሚሽኑ ተጋባዥ አሰልጣኞች የሚሰጠው ስልጠና ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን ከውሃና ኢነርጂ፣ ከግብርና፣ ከገንዘብ እና ከብሔራዊ ስትራቴጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።