ሁለተኛው የኢትዮጵያ ታዳሽ ኢነርጂ ሰሚት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

ሁለተኛው የኢትዮጵያ ታዳሽ ኢነርጂ ሰሚት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።

አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 5 ቀን 2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ)

“የኢትዮጵያን የታዳሽ ኢነርጂ ሽግግር በኢንቨስትመንት፣ በፈጠራና በትብብር ማፋጠን” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሁለተኛው የኢትዮጵያ ታዳሽ ኢነርጂ ሰሚት (Ethiopian Renewable Energy Summit 2026) ከጥቅምት 5 እስከ 7 ቀን 2019 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚገኘው Addis International Convention Center (AAICC) የስብሰባ ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።

ይህ ታላቅ ሰሚት የታዳሽ ኢነርጂ ልማትን ለማስፋፋት፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከርና በዘርፉ ያለውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማበረታታት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በሰሚቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽንና የኢነርጂ መረጃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ዳቢ፣ አገሪቱ ያስቀመጠችውን የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ግብ ለማሳካት ጠንካራ ትብብር፣ ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንትና የጎላ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆናቸውን አስረድተዋል።

አቶ መስፍን አክለውም፣ ኤሌክትሪክ ለኢኮኖሚ ሽግግር፣ ለኢንዱስትሪ ዕድገት፣ ለግብርና ምርታማነትና ለህዝብ አገልግሎት መሻሻል መሠረታዊ ሚና እንዳለው በመጠቆም፤ አስተማማኝና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ኤሌክትሪክ ለሁሉም ማዳረስ ለአገሪቱ አጠቃላይ የልማት ግቦች ስኬት ቁልፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ መረብ (Grid) ርቀው ለሚገኙ ማህበረሰቦችና የንግድ ተቋማት ዘላቂ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ፡-የቤት ውስጥ የፀሐይ ኃይል አቅርቦት ሥርዓቶች (Solar Home Systems)፣አነስተኛ የኤሌክትሪክ መረቦች (Solar Mini-grids)፣ እና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ማድረግ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የታዳሽ ኢነርጂ ሀብት በአግባቡ መጠቀም የአገሪቱን የኢነርጂ ደኅንነት ከማጠናከር ባለፈ፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስመዝገብና የኢነርጂ ሥርዓቱን የመቋቋም አቅም ለማሳደግ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አቶ መስፍን ገልጸዋል።

የግሉ ዘርፍ በኢነርጂ ልማት ውስጥ የሚጫወተውን ሚና በተመለከተም፣ የግል ኩባንያዎች የሚያመጡት ካፒታል፣ ቴክኒካዊ እውቀት፣ ፈጠራና የስርጭት አቅም የታዳሽ ኢነርጂ መፍትሔዎችን በስፋት ለማዳረስ፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠርና የአገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህንንም ዳር ለማድረስ፡-ግልጽ የፖሊሲ ማዕቀፍና ተገቢ የቁጥጥር ሥርዓት፣የፋይናንስና የውጭ ምንዛሬ ተደራሽነት፣ እንዲሁም በሚመለከታቸው ተቋማት መካከል ውጤታማ ቅንጅት መኖር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

መሪ ሥራ አስፈጻሚው አበክረው እንደገለጹት፣ የሰሚቱ ትክክለኛ ስኬት የሚለካው በሚካሄዱ ስብሰባዎችና በሚወጡ ፖሊሲዎች ብዛት ሳይሆን፣ በህብረተሰቡ የኑሮ መሻሻልና በኢኮኖሚው ላይ በሚያመጣው ተጨባጭ ለውጥ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከመንግሥት ተቋማት፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከፋይናንስ ተቋማትና ከልማት አጋሮች ጋር በትብብር በመሥራት ለኢትዮጵያ ተደራሽ፣ አስተማማኝ፣ ተመጣጣኝና ዘላቂ የኢነርጂ ሥርዓት ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

በሦስት ቀናት ሰሚቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎችን ማጠናከር፣ አዳዲስ የፋይናንስ አማራጮች፣ በግብርናና በሌሎች ምርታማ ዘርፎች የታዳሽ ኢነርጂ አጠቃቀም፣ እንዲሁም የአገር ውስጥ ማምረቻና የንጹሕ ኢነርጂ ገበያን ማጠናከር በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይትና የልምድ ልውውጥ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

Share this Post