የገዋ-ወርቆ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

የገዋ-ወርቆ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

ጥቅምት 05/2019 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በላይኛው አዋሽ ቤዚን ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ወዴቻ ተፋሰስ ዙሪያ አደአ ወረዳ የገዋ-ወርቆ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደርን ዕውን ለማድረግ ከሚተገበሩ ፕሮጀክቶች መካከል በሆነው በባዘርኔት ፕሮጀክት የገዋ-ወርቅ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታን አስጀምረዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ፕሮጀክቱን ባስጀመሩበት ወቅት በጎዲኖ ቀበሌ ገዋ መንደርን የመጠጥ ውሃን ጨምሮ ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ስማርት መንደር /Smart Village/ በማድረግ ለሌሎች ምሳሌ የምትሆን መንደር ለማድረግ ዕድሉን በማግኘታቸው መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

የገዋ-ወርቆ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በአራት ወራት ውስጥ የሚጠናቀቅና ከ2 ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ፕሮጀክቱ ተገንብቶ ለአገልግሎት እስከሚበቃ ድረስ የአካባቢው ማህበረሰብ በግንባታው ወቅት የሚሰሩ የልማት ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ ክቡር አቶ ሞቱማ አሳስበዋል።

ክቡር አቶ ሞቱማ አክለውም በወረዳው ለሚገነቡ መሰረተ ልማት ስራዎች ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የሚያደርገውንም ድጋፍ የሚቀጥል እንደሆነ ጠቁመው ከማህበረሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ወረዳውም ሆነ የሚመለከተው አካል እገዛ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

በመርሃ ግብሩ የባዘርኔት እና የብራይ ፕሮጀክት አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች፣ የአደአ ወረዳ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የሀገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ተሳትፈዋል።

Share this Post