የአዳማ ከተማ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አፈፃፀም 64% መድረሱ ተገለፀ፡፡

የአዳማ ከተማ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አፈፃፀም 64% መድረሱ ተገለፀ፡፡

የካቲት /2016 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ.) በግምብቹ ወረዳ እና የአዳማ ከተማ የተለያዩ የመጠጥ ውሃና ኢነርጂ ፕሮጀክቶችን የመስክ ምልከታ ማጠቃለያ ላይ የአዳማ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አፈፃፀም 64% መድረሱ ተገለፀ።

ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በሕ/ተ/ም ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የመሰረተልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና የጨፌ ኦሮሚያ የመሰረተልማት ቋሚ ኮሚቴ አስተባባሪዎች ጋር በነበራቸው የሁለት ቀን የመስክ ምልከታ ቆይታ አስመልክቶ በዋና ዋና ጉዳዮች ማብራሪያ እና ማጠቃለያ ሰጥተዋል።

የመጠጥ ውሃና የኢነርጂ ተደራሽነትን በተመለከተ የገጠር ማህበረሰብ አሰፋፈር የተበታተነ እና በአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት አመቺ ባለመሆኑ የህዝብን ፍላጎት ለማረጋገጥ ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን አስረድተው፤ ይህንን ችግሮች ለመቅረፍ የኃይል አቅርቦትን ተጠቃሚ ለማድረግ ከዋና የኤሌክትሪክ መስመር ውጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሻሻሉ የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን በማመንጨት እና በማሰራጨት በኩል ሰፊ ሥራዎች እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሀብቶቻችን ዘለቄታዊነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎችን በመጠናከር የአከባቢውን ስነምህዳር ሚዛን መጠበቅ እንደሚገባም አብራርተዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም የኢነርጂ አቅርቦቱ በመንግስት ብቻ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ስለማይቻል የግል ባለሀብቱ እና የአጋር ድርጀቶች ተሳትፎ ወሳኝነት ስለአለው ምቹ የፖሊሲ ዝግጅት መደረጉንም ገልፀዋል።

የመጠጥ ውሃን በተመለከተ ከፍተኛ ሀብት ተመድቦ ንፁህ መጠጥ ውሃ ለማደረስ ጥረት የተደረገ ቢሆንም፤ በተለያዩ ምክንያቶች የውሃ አቅርቦት መቆራረጥ መኖሩን ገልፀው ችግሩን ለመፍታት የአዳማ ከተማ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የውሃ አቅርቦት ስርአት ለመዘርጋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ የፕሮጀክቶቹ ማስፈፀሚያ መዋጮ በጀት (Matching Fund) በጊዜ እየተፈፀመ ባለመሆኑ ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ የአዳማ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተስፋ አስቆራጭ አፈፃፀም ውስጥ ተሻግሮ ዛሬ ለተመዘገበው ውጤት የውሃና ኢነርጂ አመራሮች በሰጡበት የአመራር ብቃት በአድናቆት ገልጸዋል። ከንቲባው አያይዘውም የአዳማ ከተማ ህዝብ የውሃ አቅርቦቱን በጉጉት እየተጠባበቀ በመሆኑ የሚመለከተው አካላት ሁሉ ውሃውን ተደራሽ ለማድረግ እርብርብ እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ፣ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ እና የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በየዘርፋቸው ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በሕ/ተ/ም የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና አከባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው በሚኒስቴሩ የተገኙ ውጤቶች የአመራሩ ቅንጅት ሥራ የመጣ መሆኑን ገልፀው፤ ከማችንግ ፈንድ (Matching Fund) ጋር ተያይዞ የተነሱ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴው የቤት ሥራ አድርጎ እንደሚወስደው አስረድተዋል።

Share this Post