የታችኛው አዋሽ ወንዝ የጎርፍ አደጋ ስጋትን ለመቀነስ የሚያስችል ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚደረግበት የወንዝ አመራር ስራ የውል ስምምነት ተደረገ፡፡

የታችኛው አዋሽ ወንዝ የጎርፍ አደጋ ስጋትን ለመቀነስ የሚያስችል ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚደረግበት የወንዝ አመራር ስራ የውል ስምምነት ተደረገ፡፡ ግንቦት 2/2015ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የታችኛው አዋሽ ወንዝ የጎርፍ አደጋ ስጋትን ለመቀነስ የሚያስችል ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚደረግበት የወንዝ አመራር ስራ የውል ስምምነት አደረገ፡፡ የውል ስምምነቱን ያደረጉት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ የአዋሽ ወንዝ በተደጋጋሚ በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ አካላዊና ቁሳዊ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝና ይህንንም ወደ ነበረበት ለመመለስ ከአሁን በፊት በተያዘው ዓመት ሚያዚያ ላይ በላይኛው አዋሽ ወንዝ ላይ የወንዝ አመራር ስራ ውል ተወስዶ እየተሰራ እንዳለ ጠቅሰው አሁን ላይ ከሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ ዝናብ እየጣለ ስለሚገኝ የታችኛው አዋሽ ወንዝ አደጋ ሊፈጥር በሚችልባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የአፋር ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በቀጥታ ገብቶ የወንዝ አመራር ስራውን እንድሰራ ለማድረግ የተወሰደ ውል ስምምነት ነው ብለዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴታው እንዳሉት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስራውን ለአፋር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሲሰጥ ባለው አጭር ጊዜ ስራውን ሰርቶ ህብረተሰቡን ከአደጋ መከላከል ያስችላል በሚል የታለመ ሲሆን ተቋሙ በባለቤትነት መንፈስ አደጋ ከመድረሱ በፊት አስፈላጊውን ግብዓት በማቅረብ፣ የስራ አመራሩን በማጠናከርና ጥብቅ ክትትል በማድረግ በተደጋጋሚ የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ መቀነስ የሚያስችል ስራ እንደሚሰራ ሙሉ እምነት እንደተጣለበት ገልጸዋል፡፡ የኮንትራት ውል ስምምነቱን የወሰደው የአፋር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሲሆን የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሊ ሙሳ እንዳሉት የታችኛው አዋሽ ሁለት ወረዳዎች ላይ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እያስከተለ እንደሚገኝ ጠቅሰው የወንዝ አመራር ስራውን ክልሉ እንዲሰራ መደረጉ ጥሩ አጋጣሚ እና የህዝብ ኃላፊነትም በመሆኑ ያላቸውን አቅም በመጠቀም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመመካከር ስራውን በአጭር ጊዜ በማጠናቅ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ቃል ገብተዋል፡፡

Share this Post