በብሔራዊ የውሃ ፍኖተካርታ ላይ በሚመክረው ስብሰባ ኢትዮጵያ የዉሃ ሀብት አጠቃቀም ልምድ አካፈለች፡፡

በብሔራዊ የውሃ ፍኖተካርታ ላይ በሚመክረው ስብሰባ ኢትዮጵያ የዉሃ ሀብት አጠቃቀም ልምድ አካፈለች፡፡ የካቲት 17/2015 ዓ.ም. የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት ባዘጋጀው በዙምባብዌ ሃራሪ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው በብሔራዊ የውሃ ፍኖተካርታ ላይ በሚመክረው ስብሰባ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የኢትዮጵያ የዉሃ ሀብት አጠቃቀም ልምድን በመድረኩ አጋርተዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ በመድረኩ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓትን በማስፈን የውሃ ሀብት በፍትሃዊነት ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ለዉሃ ሃብት መበልጸግ አስተዋጽኦ ማበርከቱንና የዉሃ እጥረትን መቋቋም የሚችል የክላስተር ስንዴ ግብርና ውጤታማነት በተሞክሮ ሊወሰድ እንደሚገባው አብራርተዋል፡፡ ክቡር ሚኒስተሩ በመጠጥ ዉሃ አቅርቦትና አጠቃቀም ጉዳዮች ላይም ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተለይ ከመንግስት በሚመደብ በጀትና በልማት አጋሮች በኩል የሚደረገውን ድጋፍ በማቀናጀት ዜጎችን የንጹህ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተው፤ ከኢነርጂ ልማት አኳያ የአረንጓዴ ሃይል ላይ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራ እንደሚገኝና የዉሃ ሃይል የማመንጨትና ለጎራቤት አገራትም ጭምር ሃይል የመላክ ስራዎችም እተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትሩ በደቡብና በደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያጋጠመዉን የድርቅ አደጋም ትልቅ ተጋዳሮት እንደሆነባት በመጥቀስ ኢትዮጵያ ያላትን ዉስን የዉሃ ሀብት መጠን ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑን አውስተዋል። የምክክር መድረኩ በተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት አስተባባሪነት እየተካሄደ ሲሆን፤ የአፍሪካ ሀገራት የዉሃ፣ የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሚኒስተሮችና የዘርፉ አመራሮች እየተሳተፉብት የሚገኝና የ2023 ማርች ወር ላይ በኒዉዩርክ ከተማ ለሚደረገዉ UN Water Conference ዝግጅት እዲያግዝ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

Share this Post