የውሃ አካላት ደህንነትን መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተገለፀ።
የውሃ አካላት ደህንነትን መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተገለፀ።
መጋቢት/2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) እምቦጭን በማስወገድ ሀይቆች የሚሰጡትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግልጋሎትን በዘላቂነት ለማስቀጠል የውሃ አካላት ደህንነትን መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢኮሀይድሮሎጂ ባለሙያ አቶ ወንድወሰን አበጀ ገልፀዋል።
የእምቦጭ አረም የውሃ አካላት ላይ በመጠንም በጥራትም ጉዳት ያደርሳል ያሉት አቶ ወንድወሰን አረሙ ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፋ ስለሆነ ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ በሰው ኃይልና በማሽን ለማስወገድ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ ግድቦች ውሃ የመያዝ አቅማቸው እንዳይቀንስ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቁመው፤ አረሙ በፍጥነት በመስፋፋት የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ቶሎ እንዲጠፋና ወደሌላ እንዳይዛመት ለማድረግ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የእምቦጭ አረም በሐይቆቹ እና በብዝሃህይወት ላይ የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እንዲሁም አረሙ በሚስፋፋባቸው አካባቢዎች የውሃ ተጠቃሚ የሆኑ ባለሀብቶችን ጭምር በማሳተፍ አረሙን ከውሃ አካላቱ ላይ ማስወገድ ትኩረት የሚሰጠው ተግባር እንደሆነ ገልፀዋል።
የላይኛው አዋሸ ቤዚን አስተዳደር ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ዲርባባ በበኩላቸው በቀጥታ ከወንዙ ላይ የሚጠቀሙ ባለሀብቶችና ድርጅቶችን በመለየት፤ 74.5 ሄ/ር መሬትን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ካርታ ለማዘጋጀት በቅድሚያ በቆቃ ግድብ ላይ ያለውን የእምቦጭ አረም መጠን መለየት፣ የውሃ ተጠቃሚዎችን መለየትና ከቆቃ ግድብ በቀጥታ የከርሰምድርና የገፀምድር ውሃን የሚጠቀሙ ድርጅቶች የሚጠቀሙትን የውሃ መጠንና የሚያንቀሳቅሱትን የካፒታል መጠን ከተለየ በኃላ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።
አቶ አብርሃም አያይዘውም በካርታ ዝግጅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢኮሀይድሮሎጂ ባለሙያዎች፣ የላይኛው አዋሽ ቤዚን አስተዳደር ቅ/ፅ/ቤት የቤዚን ፕላንና የውሃ አካላት ደህንነት ዴስክ ባለሙያዎች፣ የምስ/ሸዋ ውሃና ኢነርጂ መምሪያና የጎራ ወረዳ የውሃና ኢነርጂ ፅ/ቤት የተዋቀረ የቴክኒክ ቡድንና የስምጥ ሸለቆ የጂ.አይ.ኤስ ባለሙያዎችንና ካርታውን በማዘጋጀት የተባበሩትን ሁሉ አመስግነዋል።