ክቡር ሚኒስትሩ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ህብረት የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አወር ጋር ተወያዩ።

ክቡር ሚኒስትሩ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ህብረት የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አወር ጋር ተወያዩ።

መጋቢት 17/2016 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ህብረት የጀርመን አምባሳደር ስቴፍን አወር እና የሳይመንስ (SIEMENS ENERGY) ኩባንያ ተወካይ ጋር በኢነርጂ ልማት ኢንቨስትመንት ዙሪያ ተወያዩ፡፡

አምባሳደር ስቴፍን አወር ኢትዮጵያና ጀርመን የቆየ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸው፤ በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ትላልቅ ከሆኑት ድርጅቶች መካከል የሆነውን የሳይመንስ ኢነርጂ (SIEMENS ENERGY) ኩባንያ በኢትዮጵያ ያሉትን የኢነርጂ ልማት አማራጮች ላይ ለመሳተፍ ያለውን ፍላጎት ተናግረዋል፡፡

ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከዚህ በፊት በበርሊን ኢነርጂ ትራንዚሽን መድረክ መሳተፋቸውንና በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ጥሩ ተሞክሮና ልምድ መገኘቱን ተናግረው፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሃይል ትስስር መፍጠሯን ገልጸዋል፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም የሀይል አቅርቦት ብቃትና ውጤታማነት ላይ የሚያግዙ የግሉ ዘርፍ ካፓኒዎች በታዳሽ ሀይል ልማት ዘርፍ እንዲሰማሩ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን አንስተው፤ ከውሃ ሀይል፣ ከነፋስ ሀይል፣ ከጸሀይ ሀይል፤ ከጅኦተርማል ሀይል ለማመንጨት የተለያዩ ለኢንቨስትመንት የተለዩ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንና ለዚህም የመንግስትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት አዋጅ አስቻይ የህግ ማእቀፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የግሪን ሀድሮጅን ለማምረት ያለውን እምቅ አቅም አስረድተዋል፡፡

የሳይመነስ ኢነርጂ (SIEMENS ENERGY) ኩባንያ የምስራቅ አፍሪካ ም/ፕሬዝዳንት ሚ/ር ፈራንሲዮስ ዣቪየር ዱቢየስ በበኩላቸው የሳይመነስ ኢነርጂ (SIEMENS ENERGY) በአለም ግዙፍ ከሚባሉት የኢነርጂ ኩባንያዎች መካከል መሆኑን ገልጸው፤ ላለፉት ሁለት አመታት በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ሀይል የማመንጨትና አጠቃላይ ከሃይል ስራዎች ጋር ያለውን እምቅ አቅም በማየት ወደ ቀጠናው መሰማራታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሚ/ር ፈራንሲዮስ ዣቪየር ዱቢየስ አክለውም በአንዳንድ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በበመጨረሻም ክቡር አምባሳደሩ እና ልኡካቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ዲጂታል ኤግቢሽን ማእከልንና በተቋሙ እየተከናወኑ የሚገኙ የምድረግቢ ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

Share this Post