የብሔራዊ የንፁህ ማብሰያ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ዙሪያ ምክክር ተደረገ።

የብሔራዊ የንፁህ ማብሰያ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ዙሪያ ምክክር ተደረገ።

የካቲት 14/2016 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የብሔራዊ የንፁህ ማብሰያ ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ዙሪያ ምክክር ተደረገ።

መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ ሀገራችን በኢትዮጵያ የተሻሻለ የባዮማስ ምግብ ማብሰያዎችን በማስተዋወቅ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው፤ የንፁህና ኢነርጂ ቆጣቢ ማብሰያ ተደራሽነትን ሽፋን ከ10 በመቶ በታች በመሆኑ ከ90% በላይ ህዝባችን ለምግብ ማብሰያነት ጥቅም ላይ የሚውለው ማገዶ ደን በመመንጠር ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ የአፈር መሸርሸርና ደንን በማራቆት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በመቀነስ የምግብ ዋስትናችንን እንዳናረጋግጥ ከማድረጉም በላይ በምግብ ማብሰል የሚሳተፉትን ሴቶችና ህፃናትን ለጤና እክል ያጋልጣል ብለዋል።

ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ኢነርጂ ማመንጨት ብቻ ሳይሆን የመነጨውን ኢነርጂ በአግባቡ መጠቀም የኢነርጂ ብቃት ግምት ውስጥ መግባት ስላለበት የኢነርጂ ፖሊሲውን በዚህ ልክ ለማሻሻል ክለሳ መደረጉን ጠቁመው፤ ፖሊሲውን ወደታች በማውረድ ተግባራዊ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ፍኖተ ካርታው ከወራቶች በኋላ እንደሚጠናቀቅ ገልፀዋል።

በGIZ የኢነርጂ ልማት ፕሮግራም ፖሊሲ አማካሪ ዶ/ር አስቻለው ደመቀ በሀገራችን የእንጨት ማገዶ በመጠቀም የጤና ችግር፣ የደን መራቆትና መሰል ችግሮች ተጋላጭ በመሆኗ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ የልማት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ብዙ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም በዘላቂነት ውጤት ለማምጣት እ.ኤ.አ በ2030 ንፁህ የማብሰያ ቴክኖሎጂን ለማዳረስ ታሳቢ የተደረገ ፍኖተ ካርታ መሆኑን ገልፀዋል።

ዶ/ር አስቻለው አያይዘውም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ምንም እንኳን የስራው ባለቤት ቢሆንም ሚደረገው ክትትልና ድጋፍ አመስግነው GIZ, EnDev እና ሌሎች የልማት ድርጅቶች በፍኖተካርታ ዝግጅቱ ላይ እንደተሳተፉ ገልፀው ፍኖተ ካርታው ህብረተሰቡ ከማገዶ ማብሰያ ተላቆ ኢነርጂ ቆጣቢ ማብሰያ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ሲሆን በቀጣይ ለሚመለከታቸው የየክልል ባለሙያዎች በማቅረብ ከወራት በኋላ እንደሚጠናቀቅ ገልፀዋል።

Share this Post