ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ትብብርን እውን ለማድረግ ግንባርቀደምነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተገለጸ፡፡
ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ትብብርን እውን ለማድረግ ግንባርቀደምነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተገለጸ፡፡
የካቲት 14/2016 ዓ.ም. (ው.ኢሚ.) በቡሩንዲ ቡጁምቡራ እየተካሄደ በሚገኘው 25ተኛው የናይል ቀን እየተሳተፉ የሚገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ ትብብርን እውን ለማድረግ ግንባቀደምነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጹ፡፡
ክቡር ሚኒሰትሩ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ለሩብ ክፍለዘመን የዘለቀው ጉዞው ሲገመገም፣ በ25 ዓመታት ጥሩ ውጤቶችን አምጥቷል ብሎ መናገር እንደሚቻል አንስተው፤ በተለይ በተወሰኑ የተፋሰሱ አካባቢዎች የልማት ስራዎችን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።
ምንምን እንኳን ህጋዊ አካልነት ባያገኝም፤ በአባል ሀገራት መካከል የውውይት ፎረሞችን በመፍጠር፣ የአቅም ግንባታ ስራዎችን በማከናወን፤ ስለተፋሰሱ ግንዛቤ በማስጨበጥና የተፋሰሱ የእውቀት ምንጭ በመሆን፤ እንዲሁም የናይል ጉዳዮችንና የትብብር አስፈላጊነትን ለአለምአቀፉ ማህበረሰብ የማስተዋወቅ ስራ በማከናወን አበረታች ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸው፤ ናይል ቤዚን ኢኒሸቲቭ 25 አመታት ቢያስቆጥርም እስከአሁን የሽግግር መሳሪያ ብቻ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ተናግረዋል፤
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም ቋሚ ህጋዊና ተቋማዊ ማእቀፍ በፍጹም ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆን አንስተው፤ ቋሚ ህጋዊ እና ተቋማዊ ማእቀፍ የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት አስተዋጽኦና ተሳትፎ ቋሚና ወጥ እንዲሆንና በአባል ሀገራት የመንግስታት መቀያየር ምክንያት ተጽእኖ ውስጥ የማይወድቅ ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል፡፡
ይህ የብርዮ በልዩ በዓል አባል ሀገራት የናይል ተፋሰስ የትብብር ማእቀፍ ስምምነትን በማጽደቅ ወደፊት ለመራመድ ወሳኝ ሰዓት መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያም የናይል ተፋሰስ ትብብርን እውን ለማድረግ ግንባርቀደምነቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የትብብር ልማትን በተመለከተ በአባል ሀገራት መካከልና በናይል ተፋሰስ የሚገኙ ህዝቦች ክፍተኛ የመልማት ፍላጎት ቢኖርም፤ የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ የልማት አጀንዳ ሊረጋገጥ አለመቻሉን ጠቅሰው፤ በዝግጅት ሂደት ላይ የሚገኘው የናይል ተፋሰስ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም የናይል ተፋሰስ ህዝቦችን ፍላጎት ለማሟላት፤ ብሎም ህይወታቸውን ለመቀየር መልካም አጋጣሚ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ካለፉት የናይል ቤዝን ኢኒሼቲቭ መረዳት እንደሚቻለው፤ በናይል ተፋሰስ ተጨባጭ ሁኔታ ከውጭ በሚደረጉ የፋይናንስ ድጋፎች ላይ ብቻ በመመርኮዝ ትልልቅ የልማት ስራዎችን ለማከናወን አዋጭ ሆኖ አይታይም ያሉት ክቡር ሚነስትሩ፤ የውስጥ አቅምን ተጠቅሞ ሀብት በማሰባሰብ የተዘጋጁ የኢንቨስትመንት ፕጀክቶችን መተግበር ይገባል ብለዋል፡፡