የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ እና ከዴንማርክ ኢምባሲ ጋር ተቋማዊ አቅም ግንባታ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃግብር አካሄደ፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ እና ከዴንማርክ ኢምባሲ ጋር ተቋማዊ አቅም ግንባታ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃግብር አካሄደ፡፡ ህዳር 11/2016 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ.) የውሃና የኢነርጂ ሚኒስቴር ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ ጋር የከርሰ ምድር ውሃ ጥናት ፕሮጀክት፤ እንዲሁም ከዴንማርክ ኢምባሲ ጋር ውሃ ተኮር ስትራቴጂካዊ ትብብር ፕሮግራም ላይ የማስጀመሪያ መርሃብር አካሄደ። የማስጀመሪያ መርሃግብሩን በንግግር የከፈቱት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሃይድሮሎጂና ተፋሰስ መረጃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ እንደተናገሩት፤ በአጋርነት የሚከናወኑ ሥራዎች በውሃ ሀብት አስተዳደር ላይ የላቀ ውጤት እንደሚያመጣ ገልፀዋል። የተቋማዊ አቅም ግንባታ ፕሮጀክት አላማ በሀዋሳ፣ በድሬዳዋ እና በሀረር ከተማ መስተዳደሮች የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት መረጃዎችን በዘመናዊ በማደራጀት ተቋማዊ አቅም ግንባታን ማጠናከር እና በሂደቱም ከፈረንሳይና ዴንማርክ ልምድ ልውውጥና የእውቀት ሽግግር እንደሚኖር አቶ ደበበ ደፈርሶ ገልፀዋል፡፡ በኢትዮጵያ የውሃ ሀብትን በአግባቡ የማስተዳደር አስፈላጊነትን ያስታወሱት መሪ ስራ አስፈጻሚው፤ የውሃ ሀብታችን አሳታፊ፣ ዘላቂ እና ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የህግ ማዕቀፎች የተዘጋጁ ቢሆንም፤ የአቅም ውስንነቶች መኖሩን ጠቅሰው፤ ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ እና ከዴንማርክ ኢምባሲ የተገኙ የአቅም ግንባታ ድጋፍ የአቅም ችግሮቻችንን ይቀርፋል ብለዋል። አያይዘውም የከርሰ ምድር ውሃ ሀብትን የማቀድ የማስተባበር እና የመቆጣጠር የሚኒስቴሩን አቅም ያሳድጋል ብለዋል።

Share this Post