አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አንድ አመት ያስቆጠረው የሶላር ኢነርጂ ማቀዝቀዣ ውጤታማ ነው ሲሉ ማህበራቱ ገለጹ፡፡

አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አንድ አመት ያስቆጠረው የሶላር ኢነርጂ ማቀዝቀዣ ውጤታማ ነው ሲሉ ማህበራቱ ገለጹ፡፡ ህዳር 11/2016ዓም (ው.ኢ.ሚ) በውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአማራጭ ኢነርጂ ዘርፍ ከጅአይ ዜድ (GIZ) ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ከሚተገበሩ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ ለኩ ቀበሌ የተተከለው እና ለጣራሚሶና አካባቢ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራችና አቅራቢ ማህበር የተላለፈው የአትክልትና ፍራፍሬ የሶላር ኢነርጂ ማቀዝቀዣ ፕሮጀክት ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ ፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ክፍል በስፍራው ተገኝቶ እንደተመለከተው ማህበራቱ 50 አባላት ያሉት ሲሆን አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማምረት ወደ ገበያ እስከሚቀረብ ድረስ በማቀዝቀዣው በማስቀመጥና በማቆየት ምርቱ ሳይበላሽ ለገበያ የሚቀርብበት ሂደት መኖሩን ለማረጋገጥ ተችሏል ፡፡ በሸበዲኖ ወረዳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደበበ ዳበረ በስፍራው ተገኝተው በሰጡን ቃለ ምልልስ አካባቢው የመስኖ አቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰው ማህበራቱ በሶስት ቀበሌዎች የሚገኘውን ምርት በመሰብሰብ ወደ ገበያ እስከሚቀርብ ድረስ አቀዝቅዞ በማቆየት ከአሁን በፊት ይበላሽባቸው የነበረውን ምርት እንዳይበላሽ በማድረግ ተጠቃሚነታቸው በእጅጉ እንደጨመረላቸው ገልጸዋል፡፡ አክለውም እንደወረዳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ማህበራቱን በቅርብ በመከታተል በመደገፍ እገዛ እያደረጉ መሆኑንና ከማሽን ጥገና አንጻርም ከወረዳው እስከ ክልል ድረስ በተዘረጋው ሰንሰለት ችግሩ የሚፈታበት ስርዓት አለ ብለዋል፡፡ የህብረት ስራ ማህበሩ ዋና ሰብሳቢ አቶ ኩየሬ ወሬሶ እንደገለጹት ደግሞ አሁን ላይ የሶላር ኢነርጂ ማቀዝቀዣ ማሽኑ ለማህበራቱ መሠጠቱ የምርት መበላሸት ሳይኖር ተረጋግተን ገበያ በማፈላለግ በጥሩ ዋጋ እየሸጥን ስለሆነ ትርፋማ መሆን ችለናል ብለዋል። ከዚህም ጎን ለጎን ማህበራችን ከአትክልትና ፍራፍሬ በተጨማሪ የዶሮ እርባታ ስራን እያስፋፋ ሲሆን እንቁላሉ እንዳይበላሽ የሶላር ማቀዝቀዣ ውስጥ በማቆየት ለገበያ የምናቀርብበትን እድል አመቻችቶልናል ብለዋል። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እዚህ እንድንደርስ እና ትርፋማ እንድንሆን የሶላር ማቀዝቀዣ ድጋፍ ያደረጉልንን አካላት እና የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ማመስገን እንፈልጋለን ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

Share this Post