የንጹህ መጠጥ ውሀና ሳኒቴሽን አገልግሎት መጠናከር ለጤናው ዘርፍ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

የንጹህ መጠጥ ውሀና ሳኒቴሽን አገልግሎት መጠናከር ለጤናው ዘርፍ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ መስከረም 02/2016ዓም(ው.ኢ.ሚ )የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች እና ሰራተኞች በውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር " የውሀ ሀብታችን ለብልጽግናችን " በሚል በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን ሀገር አቀፍ አውደ ርእይ ጎበኙ፡፡ በጉብኝቱ ወቅት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አውደርእዩ አስተማሪ እና እንደ ሀገር በውሀና ኢነርጂ ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ለኢኮኖሚያዊም ሆነ ለማህበራዊ እድገታችን ትልቅ ሚና ያላቸው በርካታ ስራዎች አይተናል ብለዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለበርካታ አገልግሎቶች የሚያስፈልገውን የውሀ ሀብት ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም መጠኑን እና ጥራቱን ከመከታተል ጋር ተያይዞ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ማየት ችለናል በማለት የገለጹት ክብርት ሚኒስትሯ፤ የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት እና የሳኒቴሽን አገልግሎት ለጤናው ዘርፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። በቴክኖሎጅ ተደግፎ የከርሰ ምድር ውሀን የማወቅ እና ለልዩ ልዩ አጠቃቀም ከማዋል ጋር ተያይዘው የተሰሩ ስራዎች፤ እንዲሁም የአማራጭ ኢነርጂዎችን በመጠቀም የጤናውን ዘርፍ መደገፍ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም ክብርት ሚንስትሯ በተለያዩ የአማራጭ ኢነርጂዎች ለመጠቀም ተቋሙ እየሄደበት ያለው መንገድ ለጤና ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

Share this Post