በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።

በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ። መጋቢት / 2015 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጅ ሚኒስቴር የአባይ ቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤት በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዙሪያ በጅማ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ። የስልጠና መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት በውሃና ኢነርጅ ሚኒስቴር የአባይ ቤዚን አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ የወንደወሰን መንግሥቱ እንደገለጹት የአባይ ቤዚን ፕላን ሲዘጋጅ ለሀገራችን አዲስ ሀሳብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በርካታ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ጠቅሰው ችግሮቹን ለመፍታት አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመቀመር የቤዚን ፕላን ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት መቻሉን ገልፀዋል። ቤዚን ፕላኑን ለማዘጋጀት፤ በተፋሰሱ ውስጥ ያሉ አቅሞች እና ተግዳሮቶች ዙሪያ የሁኔታ ዳሰሳ ሥራዎችን መሰራታቸውን ገልጸው፤ የአከባቢ ሁኔታ፣ የውሃ ሀብት አቅም፣ የተቋማዊና ህጋዊ ሁኔታና የአደጋ ስጋት ትንተናዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል። በሌላ በኩል በውሃና ኢነርጅ ሚኒስቴር የሃይድሮሎጂ እና የተፋሰስ መረጃ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ እንደገለጹት የመርሀ ግብሩ ዋና ዓላማ በየደረጃው ያለው ባለድርሻ አካላት የተፋሰስ እቅድ ትግበራ ትውውቅ ለማድረግ እና እቅዶችን በቤዚን ደረጃ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር የታሰበ መሆኑን አውስተው፤ የቤዚን እቅዱ ሦስት የትኩረት መስኮች ማካተቱን፤ የትኩረት መስኮቹም የአከባቢ ደህንነት ጥበቃ፣ የውሃ ሀብት አስተዳደር እና የተቋማዊ አደረጃጀት ዋናዎቹ መሆናቸውን አስረድተዋል። መሪ ስራ አስፈጻሚው አክለውም ቅንጅታዊ አሰራር ቁልፍ ችግር እንደሆነ ጠቅሰው፤ መድረኩ ቅንጅታዊ የአሰራር ችግሮችን በመቅረፍ በባለድርሻ አካላት መካከል የረጅም ጊዜ የጋራ እይታ መፍጠር እንደሚያስችል ገልፀዋል።

Share this Post