ተቋሙ ከኦሮሚያ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመተባበር በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዙሪያ ስልጠና አካሄደ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመተባበር በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዙሪያ ስልጠና መርሃ ግብር አካሄደ። መጋቢት 18/ 2015 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ጋር በመተባበር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሥርዓትን በማስፈን የዜጎች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያስችላል የተባለውን የምክክር እና የስልጠና መርሀ ግብር በአዳማ ገልመ አባገዳ ማካሄድ ጀመረ ። የምክክር መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት በውሃና ኢነርጅ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ እንዳሉት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ተቋማዊ ሪፎርም መደረጉን አስታውሰው የሀገሪቷን የውሃ ሀብት በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል፤ ዘመናዊ የውሃ ሀብት አስተዳደር ሥርዓት ማስፈን፤ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የሳኒቴሽን አገልግሎት ተደራሽነት ማስፋፋት እና የኢነርጂ ልማት ማዳረስ በሚያስችል መልኩ መደራጀቱን ገልፀዋል። በሀገሪቱ በቂ ዓመታዊ የዝናብ ወቅት፣ ወንዞችና ሐይቆች ያሏት ቢሆንም የዝናብ መጠኑ በቦታውና በጊዜ ያለው ስርጭት የተዛባ መሆኑን ጠቅሰው፤ የውሃ አካላት በተፈጥሮ ሀብት መራቆት፤ የአየር ንብረት ለውጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ህብረተሰቡን በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ማድረግ አለመቻሉን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል። ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም እነዚህ ተግዳሮቶችን ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ውሃን ማዕከል አድርጎ የተናበበ፣ ሁሉን ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ እቅድ፣ የትግበራ እና የክትትልና ግምገማ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል። በመጨረሻም ሁሉም የሥልጠናው ተሳታፊዎች በመነሻነት በሚቀርቡ የስልጠና ፅሁፎች ላይ የየራሳቸውን እውቀት እና ልምድ በመጨመር በውሃ ሀብት አስተዳደር መስክ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲተጉ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በመጀመሪያ ቀን የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ገለፃዎች የቀረበ ሲሆን በነገው ዕለት በሁለት ቡድን በቀረቡት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሄዷል።

Share this Post