8ኛው የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን ፎረም ተጠናቀቀ፡፡

8ኛው የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን ፎረም ተጠናቀቀ፡፡ መጋቢት 29/2015 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ ያዘጋጁት 8ኛው የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲና ኮሙኒኬሽን ፎረም ተጠናቀቀ፡፡ በመርሃግብሩ በማጠቃለያ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉን ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎች መቅረባቸውንና በእለቱም ተመሳሳይ ስራዎች መቅረባቸውን ገልጸዋል። ክቡር ሚ/ር ዴኤታው ወደፊት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት ስምምነቶችን በመፈራረም ከሚዲያው ጀምሮ በውሃው ዘርፍ በርካታ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባና የተግባቦት ሂደቱም በጥንቃቄ ሊተገበር እንደሚገባ አውስተዋል። በመድረኩ እንደተገለጸው ፎረሙ አጠቃላይ የውሃ ሀብታችን ላይ ያለውን ብዥታ የሚያጠራ መሆኑንና እንደሀገር ያለንን ሀቅ ለማድረስ እድል እንደሚፈጥር ተነግሯል። ቀጣዩ ፎረም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት የሚካሄድ ይሆናል።

Share this Post