127ኛው የአድዋ ድል በዓል ተከበረ።

127ኛው የአድዋ ድል በዓል ተከበረ። የካቲት 22/2015ዓ.ም (ውኢሚ) 127ኛው የአደዋ የድል በዓል በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ፡፡ በበዓሉ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ የአደዋ ድል ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት ፣ የነጻነት ተምሳሌት መሆኑን ብሎም ጣሊያንን በማሸነፍ ሂደት በአለም አደባባይ ቀና ብለን እንድንሄድ ከማድረጉም በላይ የሴቶች የአመራር ጥበብ የታየበት ድላችን ነው ብለዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ከአያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን የወረስነውን ጀግንነት፣ አንድነትና ጽናት አሁን ላይ ህይወት ለመክፈል ሳይሆን ሁላችንም በተሰጠን ሀላፊነት ከሚያለያዩን ነገር ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ አገራችንን ወደ ተሻለ ደረጃ የምናሸጋግርበት ነው ብለዋል፡፡ የአደዋ ጦርነት መንስኤ እና የጦርነቱ ሂደት በሚል ርእስ የተዘጋጀ የመወያያ ሰነድ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስነምግባር እና ጸረ-ሙስና ስራ አስፈጻሚ በአቶ ጌትነት ስሜ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን የሻማ ማብራት፣ የዳቦ ቆረሳ፣ ስነጽሁፍና የጥያቄና መልስ ውድድር ደግሞ በዓሉን ካደመቁት ዝግጅቶች የሚጠቀሱ ናቸው።

Share this Post