120 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጭ በኦሞ ወንዝ ላይ እየተከናወነ የሚገኘው የወንዝ አመራር ስራ ተጎበኘ።

120 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጭ በኦሞ ወንዝ ላይ እየተከናወነ የሚገኘው የወንዝ አመራር ስራ ተጎበኘ። ግንቦት 7/2015አ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የሚመራ የከፍተኛ አመራሮችና የባለሙያዎች ቡድን በደቡብ ኦሞ ዞን በዳሰነች ወረዳ በኦሞ ወንዝ ላይ 120 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ እየተከናወነ የሚገኘውን የወንዝ አመራር ስራን ጎብኝተዋል። ክቡር ሚኒስትሩ በኦሞ ወንዝ ላይ እየተሰራ ያለውን የወንዝ አመራር ስራን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ መጠይቅ የክረምት ወራትን ተከትሎ የኦሞ ወንዝ በመሙላት በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለና ከቀያቸው እያፈናቀለ እንደሚገኝ ጠቅሰው ይህን ከኦሞ ወንዝ የሚወጣውን ትርፍ ውሃ ጉዳት እንዳያደርስ አቅጣጫውን በማስቀየር ለልማት እንዲውል ለማድረግ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጀምሮ በየደረጃው እስከ ወረዳ ድረስ በጋራ በመሆን ከ12 ኪ.ሜ በላይ የወንዝ አመራር ስራ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ማህበረሰቡ ወደ ቀየው የሚመለስበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠርና መሬቱም በአግባቡ ለሚፈለገው አገልግሎት ማዋል እንደሚቻል ገልጸዋል። ጎርፍ በአግባቡ ከተጠቀምንበት እድል ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ የውሃ ማኔጅመንት ስራውን በሚገባ በመምራት የውሃ ሀብታችን ተጠቅመን ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ከቻልን ጎርፍ ሀብታችን ነው ብለን የምናምንበት ጀረጃ ላይ እንደርሳለን ብለዋል። ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም የወንዝ አመራር ስራው በመሀንዲሶቻችን አማካኝነት በማሽን ኪራይ ብቻ እንዲሰራ መደረጉ ውል ቢሰጥ እስከ 400 ሚሊየን የሚደርስ ከእጥፍ በላይ ወጪን ለመቀነስ እንደተቻለም ገልጸዋል። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ በበኩላቸው የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ ከተመረጡ ተፋሰሶች አንዱ የኦሞ ተፋሰስ መሆኑንና የወንዙ መሙላት በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት እያስከተለ የቆየ መሆኑን ጠቅሰው ይህ ሀብት ውሃን መሰረት አድርገው ለሚያለሙ በጣም ጠቃሚ በመሆኑ አሁን ባለበት ሁኔታ ሊያስከትል የሚችለውን ስጋት ለመቀነስ የሚያስችል የአጭር ጊዜ የወንዝ አመራር ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የወንዝ አመራር ስራው በመሰራቱም ከ10 በላይ የሚሆኑ ቀበሌዎችን ከመፈናቀል የሚታደግ መሆኑንና 30 የሚጠጉ ቀበሌዎች ነዋሪዎችን ደግሞ ከጎርፍ አደጋ ስጋት የሚታደግ ነው ብለዋል። ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ፕሮጀክቱ በ60 ቀናት ውስጥ ተጠናቆ ለሚፈለገው አገልግሎት እንደሚውልና በቀጣይ የሚከናወኑ ስራዎችም መርሃግብር ወጥቶላቸው የሚተገበሩ ይሆናል ብለዋል። የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅረማሪያም አመነ እንዳሉትም የኦሞ ወንዝ ከ98ሺ ሄክታር በላይ መሬት በውሃው መያዙንና ከ62 ሺ በላይ ማህበረሰቦችን ማፈናቀሉን ጠቅሰው ፕሮጀክቱ ውሃውን በመቀነስ በመደበኛ ሁኔታ እንዲፈስ በማድረግ በንብረትና በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በእጅጉ ከመቀነስ ባሻገር አካባቢው ዝናብ አጠር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መስኖን በማልማት እንዲጠቀሙና ለእንስሳቶችም ጥቅም እንዲሰጥ ይደረጋል፤ የሚደርሰውንም አደጋ በእጅጉ ይቀንሳል ብለዋል። አስተዳሪው አክለውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየሰራ ያለው ስራ ወሳኝ መሆኑንና እንደ ወረዳም በየጊዜው እየተከታተሉ በጋራ የመደገፍ ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል። የወንዝ አመራር ስራው ሲጠናቀቅ እስከ አንድ ሚሊየን የሚገመት የእስሳት ሀብት ከጉዳት እንደሚታደግና አካባቢው ላይ 30 በመቶ እንቅስቃሴ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተገልጿል።

Share this Post