ለስራ ክፍሎች የእቅድ ተወካዮች (Planning focal Persons) በእቅድ ዝግጅት፤ ክትትልና ግምገማ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ።

ለስራ ክፍሎች እቅድ ተወካዮች (planning Focal persons)  በእቅድ ዝግጅት፣ክትትልና ግምገማ ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
ህዳር 02/2015 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለስራ ክፍል ተወካዮች በእቅድ ዝግጅት፤ክትትልና ግምገማ ዙሪያ ከጥቅምት 02—04/2015 ዓ.ም በአዳማ ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
የስልጠናውን መርሀ ግብር በንግግር የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሻ ኃይሉ ስልጠናው፤ በሁሉም ስራ አስፈፃሚ ስር ያሉትንና በየዘርፉ ላሉ ባለሙያዎች ዕቅድ ከማቀድ ጀምሮ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር እንደ ሚኒስቴር መ/ቤት እቅድና ሪፖርት ጥራትንና ግዜን የጠበቀ እንዲሁም ወጥ የሆነ የልማት ዕቅድ ለማዘጋጀት የሚያስችል አቅም የሚፈጥር እንደሆነ የመግባቢያ ውይይት ለማድረግ የታሰበና ለነገው ውጤታማ ስራ ለመስራት እንደሚያስችል ገልፀው ቁልፍ አመላካች አፈፃፀም (KPI) ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ ኖሮን በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን፤ በኢነርጂ ልማትና እና በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ በመደበኛና በቁልፍ አፈፃፀም የፕሮገራም በጀት ቀርፀን እንዴት ክትትልና ግምገማ እናደርጋለን፤ ስራችንን ባቀድነው ልክ ሰርተን ውጤታማ ለማድረግ የታሰበ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ አለሙ መንገሻ የስልጠናው አላማ እንደ ሀገር የሚሰሩ የልማት ስራዎችን ከሚያከናውኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች  አንዱ ውሃና ኢነርጂ ሲሆን በእቅድ ዝግጅት፤ ክትትል፤ ግምገማና ሪፖርት ምንነትና አዘገጃጀት ላይ የባለሙያዎችን አቅም መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ በእቅድና በሪፖርት ዙረያ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት በውስጥ አቅም እየተዘጋጀ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም በስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ ስር ያሉ ባለሙያዎች  በአዲሱ ተቋማዊ አደረጃጀት ምክንያት ለክፍሉ አዲስ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለመስጠት እንዲሁም ከየስራ ክፍሉ  አንድ አንድ ተወካይ (Focal Person) ይሄንን ስልጠና እንዲወስዱ የተደረገው የክፍሉ እቅድና ሪፖርት ለማቅረብ የተሻለ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል እንደሆነ ገልፀው እንደ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመረጃ አያያዝ ጥራትን ለማሻሻል፤ በእውቀት የዳበረና አቅሙ የተገነባ ባለሙያ ለመፍጠር ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ስልጠናው ከዋናው መስሪያ ቤት፣ ከአባይ ቤዚን አስተዳደር ፅ/ቤት፤ ከስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ቤዝን አስተዳደርና ከአዋሽ ቤዝን አስተዳደር ፅ/ቤት ተወካዮች የተሳተፉ ሲሆን ለሶስት ተከታታይ ቀናት በእቅድ ዝግጅት፤ ክትትልና ግምገማ ሪፖርት አዘገጃጀት፤ የፕሮግራም በጀት አሰራር ስርዓት፤ የክትትልና ግምገማ ስርዓት፤ የስራ አመራር መሰረታዊ ነጥቦች፤ ስትራቴጂክ ማኔጅመንትና የቁልፍ አፈፃፀም አመላካቾች ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የታሰበ ነው፡፡

Share this Post