ክቡር ሚኒስትሩ ከዴንማርክ የልማት ትብብር እና አለም አቀፍ የአየር ንብረት ፖሊሲ ሚኒስትር ዳን ጆርገንሰን (Mr.Dan Jorgenson) ጋር ተወያዩ፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ ከዴንማርክ የልማት ትብብር እና አለም አቀፍ የአየር ንብረት ፖሊሲ ሚኒስትር ዳን ጆርገንሰን (Mr.Dan Jorgenson) ጋር በኢነርጂና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ፡፡ ጥር 16/2015ዓ.ም (ውኢሚ) የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር/ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከዴንማርኩ አቻቸው ዳን ጆርገንሰን (Mr.Dan Jorgenson) ጋር በኢነርጅና የውኃ ዘርፎችና ተያያዥ በሆኑ የጋራ ጉዳዮች ላይ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ጣቢያ ቢሮ ምክክር አደረጉ፡፡ የዴንማርክና የኢትዮጵያ በኢነርጂ ልማት ላይ ትብብር ተስፋ ሰጪ የዠ መሆኑና ኢትዮጵያ የወደፊት የነፋስ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር አስፈላጊ የሆኑ የነፋስ መለኪያዎችን በመደገፍ ፣ የሀይል ማመንጫ እና ማስተላለፊያ ግንኙነቶችን በመቅረጽ ረገድ እንዲሁም የኢትዮጲያ ኤሌክትሪክ ሀይልን በአቅም ግንባታው ረገድ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የዴንማርክ መንግስት ሲደግፍ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ የዛሬው ውይይትም ሁለቱ ሀገራት በጋራ ስለሚሰሯቸው ስራዎች በተለይም በኢነርጂው ዘርፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የዴንማርክ የልማት ትብብር እና አለም አቀፍ የአየር ንብረት ፖሊሲ ሚኒስትር ዳን ጆርገንሰን (Mr.Dan Jorgenson) የከርሰ ምድር ውሃ ጥናት ላይ ድጋፍ ማድረግ እንደሚፈልጉ አሳውቀው አሰላ ላይ የተጀመረው የነፋስ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ወደ አብይ የትግበራ ምዕራፍ ለማስገባት እንዲቻል የግምገማ ሂደቱ ተጠናቆ የተደረሰበት የመጨረሻ ውጤት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ አያይዘውም በኢነርጂው ዘርፍ ከም/ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን እና ከገንዘብ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ ጋር እንደተነጋገሩበት ገልጸው ከዚህ ቀደም ሲሰሩ ከነበሩ ስራዎች በተጨማሪ ሌላ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገባ ጉዳዮች ላይም ተነጋግረዋል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በበኩላቸው በኢነርጂው ዘርፍ የኢትዮጵያ ህዝብ የሀይል ተደራሽነት ከ47% የማይበልጥ መሆኑን ጠቅሰው ቀሪውን 57% የህብረተሰብ ክፍል ለመድረስ እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲሁም ፣ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትም ከ70% ያልዘለለ እና እሱም ከተደራሽነት፣ ከጥራትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ውስንነት ያለበት መሆኑን ገልጸው እገዛ እንዲያድርጉ፤ በተለይም በመንግስት ደረጃ ትልቅ ትኩረት የተሰጠውና እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤት በ10 ዓመቱ መሪ እቅድ ተካቶ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ኢነርጂ (ከካርበን ልቀት ነጻ የሆነ የኢነርጂ አቅርቦት) ዙሪያ እየተሰራ ባለው ስራ ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል፡፡ የዴንማርክ መንግስትና ህዝብ ድጋፍ ለእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ዋጋ ያለውና ፍሬውንም በተግባር እየታየ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ በምክክሩ በኢትዮያ የዴንማርክ አምባሳደርን ጨምሮ ሌሎች ልኡካንንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል መቆጣጠሪያ የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ነበሩ፡፡

Share this Post