ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ GIZ የተሽከርካሪ ድጋፍ ተደረገ፡፡
ጥር 22/2015 ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ) GIZ ባለፉት አመታት ተግባራዊ ካደረጋቸውና ከተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች 4 ተሽከሪካሪዎችን በዛሬው ዕለት ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስረክቧል፡፡
በርክክብ መርሀ ግብሩ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ሱልጣን ወሊ እንደገለፁት ግንኙነቱ ለረጅም ጊዜ የቆየና ከ50 አመታት በላይ የዘለቀ ሲሆን በኢነርጂው ዘርፍ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እንዲቻል ከዲዛይን ጀምሮ እስከ ትግበራ ድረስ ባሉ የኢነርጂ ፕሮጀክት አፈፃፀሞች ጉልህ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልፀው ይህንን ትብብር የበለጠ በማጠናከር ኢትዮጵያ በ2030 ያቀደችውን ዘላቂ የልማት ግብ ለማሳካት የሚያስችል እንደሆነና ግንንኙነቱን የበለጠ እንደሚያጠናክር ገልፀዋል፡፡
የGIZ የአየር ንብረት ቡድን አስተባባሪ ሚ/ር ስቴቨን ሊዝባ እንደገለፁት አሁን ከሚተገበሩ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እየተጀመሩ መሆናቸውን ገልፀው የኢነርጂ ልማቱን ለማሳካት በየጊዜው በሚደረጉ ጥናቶች መሰረት ፕሮጀክቶች እንደሚተገበሩ ገልፀዋል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከGIZ ጋር በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ለገጠሩ ህዝብ ኢነርጂ ተደራሽ ለማድረግ በተሻሻሉና ዘመናዊ የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎች አቅርቦትና ስርጭት ላይ በጋራ እንደሚሰሩ ይታወቃል፡፡ ይህንን የታዳሽ ኢነርጂ በሀገሪቱ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል የጀርመን መንግስት ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመሆን የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ በሚሰሯቸው ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ማስፈፀሚያ የሚሆኑ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶችን በማመቻቸት በጋራ የሚሰሩ ሲሆን ዘመናዊ የኢነርጂ ቆጣቢ ምድጃዎች እንዲሰራጩ፣ ሶላር ማሾ፣ የቤተሰብ ሶላርና ሚኒግሪዶች እንዲሰራጩ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ ዘመናዊና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደሀገር ውስጥ በማስገባት ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ እንዲሁም በታዳሽ ኢነርጂ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን አቅም በማሳደግና የግል ሴክቴሩን ሚና ከፍ ለማድረግ በመስራት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች በማሰራጨት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
በርክክቡ ወቅት የሚኒስቴር መ/ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና ኃላፊዎች፣ የ GIZ የበላይ አመራሮችና ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ተሸከርካሪዎቹን የGIZ የኢነርጂ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ሙደቢር አናም ለክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ አስረክበዋል፡፡