ኢትዮጵያ እምቅ የታዳሽ ኤሌክትሪክ ሀይል ቢኖራትም እስካሁን ጥቅም ላይ ማዋል የተቻለው5.4 ጌጋ ዋት ብቻ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ግንቦት /2015ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) ኢትዮጵያ እምቅ የታዳሽ ኤሌክትሪክ ሀይል ቢኖራትም እስካሁን ጥቅም ላይ ማዋል የተቻለው5.4 ጌጋ ዋት ብቻ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ከሰሞኑ በክቡር ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ርኢ/ር ሀብታሙ የሚመራ የከፍተኛ አመራርና ባለሙያዎች ቡድን በደቡብ ኦሞ ዞን ተዘዋውረው ከጎበኙዋቸው የልማት ቦታዎች መካከል የኦሞራቴ የሶላር ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ አንዱ ነው።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር/ኢ/ር ሡልጣን ወሊ በጉብኝቱ ወቅት ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለመጠይቅ ሶላር ኢነርጂን ከማስፋፋት አኳያ እስካሁን በሚፈለገው ልክ ተደራሽ ለማድረግ በመንግስት ሲሰራበት የቆየ ቢሆንም ኢትዮጵያ ካላት የታዳሽ ኢነርጂ 5.4 ጌጋ ዋት ብቻ እየመነጨ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ላይ የኢነርጂ ፖሊሲ በመከለስ የግል ባለሀብቱና ድርጅቶች ሀይል በማመንጨትና በማስተላለፍ ስራው ተሳታፊ እንዲሆኑና አጋርነቱም የበለጠ እንዲጠናከር ህብረተሰቡም ተጠቃሚ እንዲሆን በተከለሰው የኢነርጂ በፖሊሲ መልስ ማግኘት መቻሉን እና በዚህም መሰረት በሁሉም ክልሎች 12 የሶላር ኢነርጂ የሙከራ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እየተደረጉ ሲሆን ከነዚህም መካከል የኦሞራቴ የሶላር ኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት አንዱ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ አሁን ላይ የኦሞራቴ ማህበረሰብ ከ14 ሰዓት በላይ በቀን መብራት ማግኘት የቻሉ ሲሆን ይህም በቂ ባለመሆኑና ፍላጎቱም ከ34 ፐርሰንት በላይ በመጨመሩ ከአለም ባንክ በተገነኘ የ216 ሚኒ ሶላር ድጋፍ የኦሞራቴ ፕሮጀክት ተጨማሪ ሶላር ኢነርጂ የሚያገኝበት እድል አለ ብለዋል፡፡
የኦሞራቴ ሶላር ኢነርጂ ሳይት ኦፕሬተርና የውጭ መስመር ዝርጋታ ቴክኒሽያን አቶ አሸናፊ ቶልቻ እንዳሉት የኦሞራቴ ማህበረሰብ ከአሁን በፊት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ባለመሆናቸው የነበሩ ችግሮችን አንስተው አሁን ላይ በቀን በቂ የሚባል አገልግሎት ቢኖርም የሙሉ ቀን አገልግሎት ለመስጠት ካለው ህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ተመጣጣኝ የሆነ የሀይል አቅርቦት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በተያዘዘ ዜናም በዞኑ እየተገነቡ ያሉ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የተጎበኙ ሲሆን የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ እንዳሉት የዞኑ 60 ፐርሰንት አካባቢ ቆላማና ዝናብ አጠር በመሆኑ ረዘም ላለ ጊዜ በውሃ እጥረት ችግር የሚጠቃ እና የመጠጥ ውሃ ሽፋኑም ከ40 ፐርሰንት በታች መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ለመቅረፍ እንደዞን አነስተኛና መለስተኛ የእጅ ጉድጓዶችንና ምጮችን ከማጎልበት ባለፈ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን መገንባት የሚያስችል የካፒታል አቅም ባለመኖሩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መንግስታዊ ያልሆኑ አጋሮችን በማስተባር በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች 14 የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ይገኛል ብለዋል፡፡
አክለውም ችግሩ በርካታ ቢሆንም ባለፉት ዓመታት ይህንን የሚመጥን እንቅስቃሴ አለመደረጉንና አሁን ላይ የፌደራል መንግስት ችግሩ ባለባቸው አካባቢዎች በርካታ ፕሮጀክቶችን እየሰራ እንደሚገኝና በዚህም መሰረት በሚቀጥሉት ዓመታት የመጠጥ ውሃ አቅርቦቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚሻሻል ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም በዝናብ ወቅት ውሃን ለመያዝ የሚያስችሉ ግድቦችን በመስራት በደረቅ ወቅት መጠቀም የሚቻልበት እድሉ እንዳለና ወንዝ በአካባቢያቸው የሌሉባቸውንና ችግሩ በስፋት ለተከሰተባችው አካባቢዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡