የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ376 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተፈራረመ፡፡

የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ376 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተፈራረመ፡፡ ጥር 2015 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሀና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ376 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለውና 60,000 ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በሲዳማ ብሔራዊ ክልል፤ ዳየ ከተማ ለማስጀመር ተፈራረመ፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ዜጎችን የንፁህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አቅርቦት ተጠቃሚ ለማድረግ፤ በጥናትና ዲዛይን፣ ግንባታና በግብዓት አቅርቦት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ የግንባታ ፕሮጀክትም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት አካባቢው የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ያለበት በመሆኑ ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ የህብረተሰቡን ችግር እንዲቀርፍ ሰፊ ስራ መስራት እንደሚገባ እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡ አምባሳደሩ አክለውም ፕሮጀክቱ ከ376 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት ከ60 ሺህ በላይ የከተማውን ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፤ የክልሉ መንግስት እና የክልሉ ውሃ ቢሮ ትኩረት በመስጠት የፕሮጀክት ስራው በታቀደው አግባብ እንዲከናወን የክትትልና ቁጥጥር ተግባራትን በሚገባ ማከናወን እንደሚገባቸው ከወዲሁ አሳስበዋል፡፡ የግንባታ ስራውንና የግብዓት አቅርቦቱን ጂቲቢ ኢንጂነሪንግ እና ኢሙ አጠቃላይ አስመጪ በጋራ የሚያከናዉኑ ሲሆን፤ ክቡር ሚኒስትር ዴዔታው እንደገለጹት የኮንትራት ስራው ድርጅቶቹ በገቡት ውል መሰረት በጥራትና በታቀደው ጊዜ አጠናቀው እንደሚያስረክቡ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ለጨለለቅቱ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን የግንባታ ፕሮጀክት የቁጥጥርና የኮንትራት አስተዳደር ማማከር ስራን እንዲያከናውን ከደቡብ ዲዛይንና ኮንስትራክሽን ቁጥጥር ድርጅት ጋር ውል ተገብቷል፡፡ በተጨማሪም በአምስት ከተሞች በከተማ አቀፍ አካታች ሳኒቴሽን (Citywide Inclusive Sanitation) በኩል በሚተገበሩ ፕሮጀክቶች አማካኝነት በአካባቢና ማህበረሰቡ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ተፅኖዎችን በመለየት ሊደርስ የሚችለውን ተፅእኖ መቀነስ የሚያስችል ዝርዝር ጥናት እንዲያካሂድ ደግሞ ከሞሽን የማማርና የስልጠና ድርጅት ጋር የውል ስምምነት ተደርጓል፡፡

Share this Post