የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለየዩ ማሽነሪዎች ከጃፓን መንግስት ተበረከተለት፡፡
ጥር/2015ዓ.ም (ውኢሚ) የኢትዮጲያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በውሃው ዘርፍ አቅም ግንባታና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ የሚገኝ መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡
ኢንስቲትዩቱ በሰው ሀይልና በማቴሪያል ራሱን ካደራጀበት ከ2008ዓ.ም ጀምሮ በመላው የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ከ7700 በላይ የውሃ ዘርፍ ባለሙያዎችበ25 የስልጠና ዘርፎች ተግባር ተኮር ስልጠናዎችን መስጠት ችሏል፡፡ ተቋሙ በውሃው ዘርፍ አቅምን በመገንባትና በቴክኖሎጂ ሽግግር በአፍሪካ የልህቀት ማእከል የመሆን ራዕዩን እውን የሚያደርግ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለውና ለስልጠናና ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ አገልግሎት የሚውል ማሽነሪ ከጃፓን መንግስት ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡
በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ የጃፓን አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ላለፉት 25 ዓመታት የውሃውን ዘርፍ አቅም በመገንባት ረገድ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው አስካሁን ባለው ሁኔታም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የውሃ ባለሙያዎች በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ቴክኒካል ስልጠና አግኝተው በክልሎች ሰፊ ስራ እየሰሩ መሆናቸውና ይህም የድጋፉ አንዱ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ክቡር አምባሳደሩ አክለውም ፕሮጀክቱ ቀጣይነት እንዲኖረው የጃፓን አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ሲሰራ የቆየ መሆኑንና የራሳችን አድረገን ማስቀጠል ስለሚገባ በቅርቡ የወጣውን ህግ መሰረት አድርገን ውስጣዊ ገቢያችንን በማጠናከር በአቅም ግንባታው፣ በምርምርና ስርጸት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በቁፋሮና በመሳለሰሉት ዙሪያ እንደሚሰራ በኮሚቴ ውይይት ተደርጎበት ስምምነት ላይ መደረሱን አብራርተው በጃፓን መንግስት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ተደርጎበት የተበረከተው የስልጠናና ቁፋሮ ማሽነሪ ትልቅ ኢንቨስትመንት መሆኑንና ውስጣዊ አቅምን የበለጠ ለማጎልበት ብሎም ቀስ በቀስ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ አጋዥ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም ራስን የመቻል አቅጣጫ ላይ ትኩረት አድርጎ ለመስራት የሚደግፍ ፕሮግራም እንደተቀረጸ አሳውቀዋል፡፡
የጃፓን አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ተወካይ ዶ/ር ካቱሱኪ ሞሪሃራ፤ የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ግንኙነት ያለውና በግብርና ፣ የግል ዘርፍ ልማት፣ በውሃ እና ሳኒቴሽን፣ የውሃ መሠረተ ልማት፣ ኢነርጂ፣ ትምህርት እና ጤናን ጨምሮ ሰፊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው በተለይም በውሃው ዘርፍ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገነቡትን የውኃ ፕሮጀክቶች ለንፁህ መጠጥ ውሃ ምቹ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ቴክኒካል ድጋፍ በማድረግ እና በሰው ሃይል ልማት ደግሞ ከኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ላለፉት 25 ዓመታት የውሃ ኢንጅነሮችንና ቴክኒሽያኖችን የውሃ ዘርፍ አቅም ለማሳደግ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ተወካዩ አክለውም ስራዎች ሲሰሩ አንዳንድ ፈተናዎች መኖራቸው እና በተለይም ከኮቪድ 19 እና ከጦርነት ጋር ተያይዞ ችግሮች የነበሩ መሆኑ ጠቁመው የስልጠናውን ጥራት ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማሻሻል በዋናነት የኢትዮጲያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የተሟላ ቁመና ያለው ተቋምነት ላይ እንዲደርስ ማደርግ አላማቸው መሆኑንና ኢኒስቲትዩቱም ያንን ለማሳካት እየሰራ እንዳለ እና እስከ መጭዉ ሰኔ ወር ድረስም የፕሮጀክት ጊዜው አንደተራዘመ ተናግረዋል፡፡
የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታመነ ሀይሉ እንዳሉትም ተቋማቸው በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት በ4 ዋና ዋና ጉዳዮች ትኩረት አድረጎ እየሰራ እንደሚገኝና የጃፓን አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ትልቅ ትኩረት አድርጎ የሚደግፈው ተግባራዊ ስልጠናው ውጤታማ እንዲሆን ለማደርግ መሆኑን ገልጸው በዛሬው እለት የተደረገውም የማሽነሪ ድጋፍ አስከ 350 ሜትር ጥልቀት መቆፈር የሚችልና የተግባር ስልጠናውን ውጤታማ ከሚያደርጉት አንዱ መሆኑንና በቀጣይም ከዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በጋራ የምንሰራቸውን የውሃ ተመራቂዎችን ብቃት ማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለንም ብለዋል፡፡
በእለቱ በኢትዮጵ ጃፓን አምባሳደር፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና ተጠሪ ተቋማት የስራ ሀላፊዎች፣ የጃፓን አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ፣ የኢንስቲትዩቱ የማኔጅመንት አባላት እና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው አካላት የተገኙ ሲሆን እስካሁን በነበረው ጉዞ የጋራ ክትትል ውጤቶች ፣ የእቅድና ድጋፍ ፣ የቀሪ የፕሮጀክት ጊዜ ተግባራት፣ የፕሮጀክት ማራዘሚያ እቅድ እንዲሁም በማሽነሪና ስልጠና አስተዳደር ዙሪያ የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዝግጅት ዙሪያ ውይይት መደረጉ የመርሃ ግብሩ አንድ አካል ነበር፡፡