በየደረጃው ያለውን አመራር አቅምን መገንባት ተቋማዊ ራዕዩን እውን ለማድረግ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለጸ፡፡

በየደረጃው ያለውን አመራር አቅምን መገንባት ተቋማዊ ራዕዩን እውን ለማድረግ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገለጸ፡፡ የካቲት /2015ዓ.ም (ውኢሚ) ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፤ የቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤትን ጨምሮ በየደረጃው ላሉ አመራሮች እና ሰራተኞች የስነምግባር መመሪያና በመሰረታዊ የስራ አመራር ተግባራት ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና በአዳማ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ የስልጠና ማስጀመሪያ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ እንዳሉት በየደረጃው ያለውን አመራር አቅምን በየጊዜው መገንባት ተቋማዊ ራዕዩን እውን ለማድረግ አስተዋጽኦ እንዳለውና በየጊዜው እየተሻሻሉና እየተዘጋጁ ለሚወጡ ደንቦች፣መመሪያዎችና የአሰራር ስርዓቶች የበለጠ ቅርብ እንድንሆን በማስቻል የመፈጸም አቅምን ያሻሽላል ብለዋል፡፡ እንደ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ተቋሙ በርካታ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱንና እየሰራ እንደሚገኝ አውስተው በእያንዳንዱ ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎችም የአቅም ግንባታውን የሚያበለጽጉ ናቸው ብለዋል፡፡ አክለውም ከአሁን በፊት በነበሩ የስልጠና ሂደቶች የታዩ ክፍተቶችን በማረም በተለይም ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም ከስልጠናው ማግኘት ያለብንን እውቀት ለመጨበጥ ስልጠናውን በሚገባ መከታተል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የስራ አመራር ምንነት እና የአመራር ክህሎት ዙሪያ የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጽሁፍ የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ በሆኑት በአቶ ኦልቀባ ባሸ የቀረበ ሲሆን የስነ ምግባር ምንነት፣ የስነምግባር መርሆዎች አፈጻጸም፣ መብቶችና ግዴታዎች፣ የስነምግባር ግድፈቶች ደረጃ እና የስብሰባ ስነስርዓት ህግን በሚመለከት የተዘጋጀ ጽሁፍ ደግሞ የስነምግባር እና ፀረ-ሙስና ስራ አስፈፃሚ በአቶ ጌትነት ስሜ ቀርቧል፡፡ ከህግ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ደግሞ በህግ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ነዒማ የቀረበ ሲሆን በአጠቃላይ በቀረቡ ጽሁፎች ዙሪያ በርካታ ሃሳቦች፣ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው በውይይት መዳበር ችለዋል፡፡ ስልጠናው በትናንትናው እለት የተጀመረ ሲሆን በዛሬው እለትም በተመሳሳይ መልኩ ቀጥሎ ይዉላል፡፡

Share this Post