የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የትብብር ማዕቀፍ የመግባቢያ ስምምነት ስነስርዓት ተካሄደ፡፡

የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የትብብር ማዕቀፍ የመግባቢያ ስምምነት ስነስርዓት ተካሄደ፡፡ የካቲት 2015ዓም (ው.ኢ.ሚ) ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከኔዘርላንድ የውሃ ቦርድ ጋር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችለውን የምዕራፍ ሁለት የትብብር ማዕቀፍ የማስጀመሪያ ስነስርዓት በካፒታል ሆቴል አካሄደ፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ እንዳሉት የውሃ ሀብታችን ካልተንከባከብነው፣ ካልጠበቅነውና በሚገባ ካላስተዳደርነው ህይወቱን የሚያጣበት እድሉ ሰፊ መሆኑን ጠቅሰው የብሉ ዲል የምእራፍ ሁለት የትብብር ስምምነት ያሉንን የውሃ ሀብቶቻችን መረጃ በሚገባ ተይዘው፣ መጠንና ጥራታቸው ተጠብቆ፣ ጥበቃ ተደርጎላቸው እና ለተጠቃሚዎች በተገቢው ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ ውሃ ላይ ከሚሰሩ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለን ነው ብለዋል፡፡ ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው አክለውም የብሉ ዲል ፕሮጀክት እንደሀገርም ሆነ እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የአቅም ግንባታ ስራው ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ በመሆኑ በውሃ ሀብት አጠቃቀም ጥሩ ልምድ ያላቸውን እንደ ኒዘር ላንድ ያሉ ሀገሮችን ተሞክሮ ለመውሰድ፣ አቅምን ለመገንባትና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል የሚፈጥር በመሆኑ በተገቢው መንገድ ከተጠቀምንበት የውሃ ሀብት አስተዳደራችን ለማዘመን የተነሳንበትን አላማ እውን ለማድረግ የማስፈጸሚያ መሳሪያ ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በምዕራፍ አንድ አፈጻጸም ወቅት የነበሩ ውስንነቶች በሚገባ ተገምግመው በሁለተኛው ምእራፍ በተጠናከረ መልኩ ለመፈጸም በሚያስችል መልኩ መረጃዎች የተዘጋጁ በመሆናቸው ተጠቃሚዎችን እና ባለድርሻዎችን በማደራጀት ብሎም በማሰልጠን ለውሃ ሀብት ልማቱ ያላቸውን ተሳትፎ የምናሳድግበት ነው ብለዋል። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ እንደገለጹት ደግሞ ሚኒስቴር መስሪ ቤቱ ያዘጋጀው የ10 ዓመት እቅድ ንጹህ የመጠጥ ውሃን ለዜጎች ማዳረስን፤ የተሻሻለ የሳኒቴሽን አቅርቦትና ፍሳሽ በአካባቢ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ ታላሚ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የብሉ ዲል ፕሮጀክት አቅም ግንባታው ላይ ትኩረት ያደረገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለሳኒቴሽን ዘርፉ አፈጻጸም የድርሻውን ለመወጣት ያለመ የትብብር ስምምነት በመሆኑ በአካባቢና በማህበረሰቡ ጤና መሻሻል ላይም አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡ የትብበር ስመምምነቱ የውሃና ኢነርጂ የበላይ አመራሮች፤ የኔዘርላንድስ ኤምባሲ አምባሳር፣ የክልል የዘርፉ አመራሮች እና ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተከናውኗል፡፡

Share this Post