የባዮጋዝ ኢነርጂ ዘርፈብዙ አገልግሎት በመስጠት ውጤት ማስገኘቱ ተገለፀ።

የባዮጋዝ ኢነርጂ ዘርፈብዙ አገልግሎት በመስጠት ውጤት ማስገኘቱ ተገለፀ። ጥር 2015 ዓ/ም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሞጆ ከተማና ዙሪያ የተሠሩ የባዮጋዝ ኢነርጂ የሥራ እንቅስቃሴ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮች እና በ/ሕ/ተ/ም/ቤት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አከባቢ እና አከባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በመሆን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ወቅት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ባዮጋዝ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተመሰገን ተፈራ እንደገለጹት የባዮጋዝ ኢነርጂ ዘርፈብዙ አገልግሎት በመስጠት ውጤት ማስገኘቱን ጠቁመው ከጤና፣ ከግብርና፣ ከአከባቢ ጥበቃ እና ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር ያለው ጠቀሜታ የጎላ እንደሆን ገልጸዋል። በመስክ ጉብኝቱ ወቀት ያነጋገርናቸው አቶ ጌታነህ አይችሉህም በሞጆ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ የባዮጋዝ ኢነርጂን የከብት እበት እና የተለያዩ ተረፈምርቶችን በመጠቀም በማምረት ለቤት መብራት እና ለምግብ ማብሰያ ከመጠቀም በሻገር ከባዮጋዝ ተረፈ ምርት የኦቮካዶ፣ የማንጎ፣ የፓፓያ እና የብርቱካን ፍራፍሬዎች በማምረት ለገበያ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል። በሌላ በኩል አቶ በዛብህ አምደብርሃን በሞጆ ከተማ በወተት ምርት የተሰማሩ ባለሀብት ሲሆኑ የባዮጋዝ ኢነርጅን በስፋት(large scale) ያመርታሉ። ባለሀብቱ እንደገለጹት የከብቶችን እበት ተጠቅሞ እስከ 60 ሜትር ኪዩብ ባዮሰላሪ የመያዝ አቅም ያለው ተገንብቶ ለቤት መብራት እና ለምግብ ማብሰያ በመጠቀም ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ባለሀብቱ እንደገለጹት በተቋማቸው የተዘጋጀው የባዮጋዝ ዳይጀስተር ከፍተኛ አቅም ያለው በመሆኑ ወደፊት የሚመረተውን የሚቴን ጋዝ ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል ለመቀየር መታቀዱን ገልጸዋል። በጉብኝቱ ወቅት የባዮጋዝ ኢነርጂ ህብረተሰቡን በኢነርጂ ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር የሴቶችን ጫና መቀነስ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሥነምህዳር ከመጠበቅ ጋር ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ የሚመለከተው ሁሉ ተቀናጅተው መስራት እንደሚገባ ተገልጿል።

Share this Post