የበጋ ወቅት የውሃ ምደባ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡

የበጋ ወቅት የውሃ ምደባ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ፡፡ ጥር 04/2015 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ፅ/ቤት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በ2015 በጀት ዓመት የበጋ ወቅት የውሃ ምደባና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በአዳማ ከተማ ውይይት አካሄደ፡፡ የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ እንደገለፁት የአዋሽ ተፋሰስ ከሚገኝበት ስትራቴጂካዊ አቀማመጥና የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አጠቃቀሞች ጋር ተያይዞ የውሃ እጥረት የሚታይበት በመሆኑ የውሃ ምደባና ክፍፍል መሰራቱ የውሃ ሀብቱን ፍትሃዊና ዘለቄታዊ ጠቀሜታ ለማረጋገጥ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ገልፀው፤ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማስፈን በሚመች መንገድ ከቤዚን ፕላን የተቀዳ የውሃ ምደባ ዕቅድ ሲሆን፤ በ2015 በጀት ዓመት የውሃ ምደባ ሂደቱ ግልፅና አሳታፊ እንዲሆን የሚያስችል አዲስ የውሃ ምደባ ዑደት ተነድፎ ተግባራዊ መደረግ መቻሉ ከውሃ ምደባ ሂደቱ የሚጠበቀውን ውጤት ከፍ የማድረግ ፋይዳ ከመኖሩም ባሻገር ልምዱን ለማስፋት አገርአቀፍና አለምአቀፍ ተሞክሮዎችን በመቀመር በአተገባበር ሂደቱ ላይ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል መድረክ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም የውሃ ምደባው የውሃ ሀብት ክፍፍል ከጊዜ አንፃር መቼ ውሃን መጠቀም እንደሚገባ፤ ከቦታ አንፃር ውሃው የሚደርስበት ቦታ፤ ከአገልግሎት አንፃር ለምን ጥቅም ይውላል፤ እንዲሁም ከተጠቃሚ አንፃር ማን የውሃ ሀብቱን መውሰድ እንደሚገባ የሚያመላክት የውሳኔ መስጫ መሳሪያ እንደሆን ገልፀዋል፡፡ የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አንድነት ጌታቸው በበኩላቸው የበጋ ወቅት የውሃ ምደባ ላይ ከባለድርሻዎች የሚነሱ ሃሳብና አስተያየቶች ለምደባው ግብዓት እንደሚሆኑና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ለምደባው ውጤታማነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡ የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ፅ/ቤት የውሃ አጠቃቀምና ፍቃድ ዴስክ ኃላፊ አቶ ጣሰው ዘውዴ እንገለፁት የበጋ ወቅት የውሃ ምደባ ለመስራት በተፋሰሱ ያሉ ሶስት ግድቦች መነሻ መሆናቸውን ገልፀው የውሃ ምደባው ዋና ዓላማ የውሃ ሃብት አጠቃቀማች ላይ ዘለቄታዊና ፍትሃዊ ክፍፍል እንዲኖር፤ ተጠቃሚው አመኔታ እንዲኖረውና እጥረት ባለበት ቦታ እንዴት በፍትሃዊነትና በቁጠባ በመጠቀም ኢፊሸንሲን መጨመር እንደሚገባ፤ እንዲሁም ምደባው አሳታፊ በመሆነ መልኩ የተሰራ ሆኖ የዋናው ተቋም ባለሙያዎች፣ የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ፅ/ቤት ባለሙያዎች፣ ከአፋርና ከኦሮሚያ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ባለሙያዎች የተሳተፉበት እንደሆነና ምደባው ከቆቃ ጀምሮ እስከ አፋምቦ ድረስ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚመለከታቸው ስራ አስፈፃሚዎች፣ ከኦሮሚያና ከአፋር የውሃና ኢነርጂ ቢሮ፣ ከግብርና ምርምር ማዕከል፣ ከመተሃራና ከሰም ስኳር ፋብሪካ፣ ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር እንዲሁም ትላልቅ የውሃ ተጠቃሚዎች የተሳተፉ ሲሆን በቀረቡት ሰነዶች ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተው ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ በመጨረሻም በውይይቱ ላይ የተነሱ ጥያቄዎችንና ገንቢ አስተያየቶችን በግብዓትነት በመውሰድ እያንዳንዱ የእቅድ ፈፃሚ አካል ድርሻውን ለይቶ ወደ ትግበራ በመግባት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ በጋራ እንዲሰሩ ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታው ከአደራ ጭምር አሳስበው ለውሃ ምደባው ተግባራዊ መሆን የክትትልና ግምገማ ኮሚቴ በማዋቀር ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

Share this Post